ፊቼ ጫምባላላ በዓልን በዩኔስኮ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚረዳ ጥናት ተጠናቀቀ

-    ሐቻምና ዲዛይኑ የተጠናቀቀው የደቡብ ባህል ማዕከል ግንባታ እስካሁን አልተጀመረም

ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች አንዱ የሆነው የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ (ፊቼ) በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጀት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተመለከተ፡፡
የሲዳማ ብሔር ባህልና ማንነት መገለጫ የሆነው የፊቼ በዓል የዓመቱ አዋቂዎች (አያንቶ) በሚወስኑት ቀንና ወር የሚውል ሲሆን፣ የዘንድሮ ዘመን መለወጫ ሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ድምቀት ተከብሯል፡፡ 

በዋዜማው በርችት ሕብረ ቀለማት ተጀምሮ በዕለቱ ከጧት ጀምሮ በባህላዊ መሰብሰቢያ ሥፍራው (ጉዱማሌ ፓርክ) የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የብሔሩ ተወላጆች፣ ቱሪስቶችና የክብር እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ ክብረ በዓሉ በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚያስችል ጥናት ተጠናቅቆ በሚቀጥለው ዓመት ለዩኔስኮ እንደሚቀርብ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል፡፡

ስለዘንድሮው ፊቼ በዓልና በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ስለሚገኘው እንቅስቃሴ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በየዓመቱ እንደሚደረገው በዓሉ ከዘመን መለወጫና በማግስቱ ጫምባላላ አዋቂዎች፣ ወጣት ሴቶችና ወንዶች በልዩ ጭፈራ (ቄጠላ) ታጅቦ እንደሚቀጥል ይናገራሉ፡፡ በየዓመቱ የፊቼ በዓል ዕለትና ወሩ መለያያትን በተመለከተም ‹‹የሲዳማ ጊዜ አቆጣጠር ከጨረቃ ሥርዓት ጋር የተገኘና ከዋክብትና ጨረቃን በመመልከትም የሚተነትኑ አዋቂዎች (በአካባቢው አጠራር አያንቶ) የሚወስን በመሆኑ ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የሲዳማ ዘመን መለወጫ (ፊቼ) ከጥንት ጀምሮ ሊከበር የመጣና የራሱ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ያሉት በመሆኑ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር ጥናት መደረጉንና በዞኑ እንቅስቃሴ የተጀመረውም ባለፈው ዓመት መሆኑን አቶ ሚሊዮን አብራርተዋል፡፡

የፊቼ ክብረ በዓል በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥናቱ ተጠናቆ በሚቀጥለው ዓመት ጥያቄው ለድርጅቱ እንደሚቀርብ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ የሲዳማ ብሔር የራሱ የቀን መቁጠሪያ (ካሌንደር) ያለው ሲሆን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን የአዲሱ ዓመት መጀመሪያና የዘመን መለዋጫ ዕለት እንደሆነ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል የደቡብ ክልል በብሔረሰቦች ምክር ቤት ዲዛይኑ ተጠንቶ ከሦስት ዓመት በፊት የተጠናቀቀው የባህል ማዕከል ግንባታ እስከዛሬ አለመጀመሩ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በባለቤትነት እንዲያስገነባ ኃላፊነት የተሰጠው የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ቢዘገይም በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 
‹‹ዲዛይኑ እንደገና ይታያል፡፡ የቦታ ዝግጅትም ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ወደ ግንባታ ለማግባት ዕቅድ ተይዟል›› በማለት የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የቢሮው አንድ ኃላፊ ለዚህን ያህል ጊዜ ግንባታው አለመጀመር የፋይናንስ አቅም ውስንነት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ ዲዛይኑን አስጠንተው ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ግንባታ ሒደት እንዲገቡ ለባህልና ቱሪዝም ቢሮ ማስረከባቸውን ለሪፖርተር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር