ሲዳማን ጨምሮ በደቡብ ክልል 960 የግብይት ማዕከላት አዲስ ግንባታናየማጠናከር ስራ ተከናወነ

ሃዋሳ ሐምሌ 19/2005 በደቡብ ክልል በተጠናቀቀዉ በጀት አመት 960 ዘመናዊ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላት አዲስ ግንባታና የማጠናከር ስራ በመከናወናቸዉ ለግብይት ስረአቱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የክልሉ ግብይትና ህብረት ስራ ቢሮ አስታወቀ ። በበጀት አመቱ ከክልሉ 11ሚሊዮን ያህል የቁም እንስሳትና ቆዳና ሌጦ ለገበያ መቅረቡም ተመልክቷል፡፡ የቢሮው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ መላኩ እንዳለ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የማዕከላቱ ስራ ህገ ወጥነትን ለመቆጣጠር እንዲሁም ቀልጣፋና ቀጣይነት ያለው የግብይት ስርዓት መፍጠር ነዉ ። ፡በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በበጀት አመቱ ከተሰሩት ከእነዚህ ማዕከላት መካከል 283 አዲስ ግንባታዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 677 ደግሞ የማጠናከር ተግባራት የተካሄደላቸዉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በመንግስትና በግል ባለሀብቶች ወጪ የተከናወኑ ማእከላት እያንዳንዳቸውም ከግማሽ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር የፈጁ መሆናቸውን አሰረድተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በመተባበር የተሰሩት የግብይት ማዕከላቱ የጥራት ደረጃተቸውን የጠበቀ የቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የጥራጥሬ፣ የቅመማ ቅመም፣ የቁም እንስሳትና ሌሎችንም የግብርና ምርቶች እየቀረቡባቸዉ መሆኑም ተመልክቷል ። ማእከላቱ በተጨማሪ መረጃዎችን በማቅረብ የአምራቹንና የሸማቹን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዙም አመልክተዋል፡፡ የግብርና ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በአይነትና በብዛት ለገበያ እንዲቀርቡና ህገ ወጥነትን ለመከላከል ለግብይት ተዋናያዎች 3ሺህ341 አዲስ የብቃት ማረጋገጫና ለ7ሺህ269 የነባር ፈቃድ እድሳት መከናወኑም የስራ ሂደቱ ባለቤት ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የገበያ መረጃን አሰባስቦ በማጠናቀር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለተጠቃሚው መልሶ በማድረስ የሚታየውን የገበያ ልዩነት ለማጥበብ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከዚህ ሌላ በበጀት አመቱ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የህብረት ስራ ማህበራትና ግለሰቦች አማካኝነት 8ነጠብ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ የቁም እንስሳት እንዲሁም ከ2ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቆዳና ሌጦ ለአካባቢውና ለማዕከላዊ ገበያ መቀረቡንም አቶ መላኩ ገልጠዋል ። በተጨማሪም ከ5 ሚሊዮን 900ሺህ ቶን በላይ የአገዳ፣ የብርእ፣ የጥራጥሬ፣ የቅባት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእጣንና ሙጫ ፣ የወተትና ሌሎችም የግብርና ምርቶች በተመሳሳይ ለገበያ በማቅረብ የግብይት ተሳታፊዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር