የደቡብ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን በተያዘው በጀት አመት ከ86 በመቶ በላይ ለማድረስ ታቅዷል

አዋሳ ሐምሌ 19/2005 የደቡብ ክልልን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን በተያዘው የበጀት አመት ውስጥ በአማካኝ ከ86 በመቶ በላይ ለማድረስ መታቀዱን የክልሉ ውሃ ሀብት ቢሮ ገለጸ፡፡ ይህንንም ለማሰካት በዘመኑ ለሚገነቡ የውሃ ተቋማት ማስፈጸሚያ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በእቅድ ተይዛል፡፡ የቢሮው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለሙያ አቶ ጁሲ ጥላሁን ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በእቅዱ መሰረት በክልል ደረጃ 1 ሺህ 183 አዳዲስ የውሃ ተቋማት ግንባታና የ172 ነባር የመጠጥ ውሃ ተቋማት የማጠናቀቅ ስራ እንዲሁም በአገልገሎት ብዛት የተጎዱ 461 የውሃ ተቋማት ከባድ ጥገና ይካሄዳሉ፡፡ በተጨማሪም ህብረተሰቡን በማስተባበር ጭምር 5 ሺህ 855 የውሃ ተቋማት በዞንና በወረዳዎች አቅም ለመገንባት በዘመኑ ከሚከናወኑት መካከል እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡ በበጀት አመቱ ለማከናወን የታቀዱት እነዚህ የውሃ ተቋማት ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በከተማ 792 ሺህ 885 በገጠር ደግሞ 4 ሚሊዮን 738 ሺህ 880 ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በማድረግ የክልሉን ሽፋን በከተማ አሁን ካለበት 79 በመቶ ወደ 91 በመቶ በገጠር ከ54 ወደ 81 ነጥብ 86 በመቶ ለማደረስ እንደሚያስችሉ አመልክተዋል፡፡ በፍሎራይድ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የስድስት ተቋማትን የፍሎራይድ ማጣሪያ በመጠገንና ተጨማሪ ማስፋፊያ በመስራት ለአገልገሎት እንደሚበቁም አስረድተዋል፡፡ የውሃ ሀብት እጥረትና ብክለት ችግር ጎልቶ በሚታይባቸው በተመረጡ አራት ንዑስ ተፋሰሶች የውሃ ሀብት አጠቃቀምና የብክለት ቁጥጥር ጥናት ማካሄድ፣ የከርሰ ምድር ውሃ መረጃ ማሰባሰብ፣ የማደራጀትና ወለል ካርታ ማዘጋጀትና የቤተሰብ መጠጥ ውሃ አቅረቦት ሳኒቴሽንና ሀይጂን የማጠናቀሩን ስራ በማጠናቀቅ በ2005 በጀት አመት የተገነቡ የውሃ ተቋማት መረጃን በማካተት የሽፋን ስሌት ወቅታዊ የማድረግ ስራም እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡ በዘመኑ ለሚከናወኑት ለእነዚህ ተግባራት ማስፈጸሚያ ከተለያዩ የገንዘብ ምንጮች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በእቅድ መያዙን ባለሙያው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር