ለዝዋይ - ሐዋሳ መንገድ ግንባታ የዓለም ባንክና ቻይና 750 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተጠየቁ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የአገሪቱን የመንገድ አውታር ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳሉ ካላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ከዝዋይ ሐዋሳ ድረስ ለሚገነባው የፍጥነት መንገድ፣ የዓለም ባንክና የቻይናው ኤግዚም ባንክ 750 ሚሊዮን ዶላር እንዲያበድሩት ጠየቀ፡፡
ባለሥልጣኑ የብድር ጥያቄውን ባለፈው ሰኞ ለዓለም ባንክ ሲያቀርብ፣ በሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ ለቻይናው ኤግዚም ባንክ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

ይህ መንገድ ከሞጆ ከተማ ተነስቶ እስከ ሐዋሳ ድረስ የሚዘረጋው ባለ አራት ረድፍ (ሌን) አዲስ መንገድ አካል ነው፡፡ ከሞጆ እስከ ዝዋይ ድረስ ለሚዘልቀው የመጀመሪያ ዙር መንገድ ግንባታ የአፍሪካ ልማት ባንክና የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ብድር ለመስጠት ፈቃደኛነታቸውን ማሳየታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት ለዚህ ግንባታ የአፍሪካ ልማት ባንክ 350 ሚሊዮን ዶላር፣ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ብድር እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ የሚቀጥለው ክፍል ማለትም ከዝዋይ እስከ ሐዋሳ የሚዘልቀው መንገድ 750 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ለዓለም ባንክና ለቻይና ኤግዚም ባንክ ቀርቧል፡፡ የሁለቱ ፋይናንስ ተቋማት ምላሽ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እንደሚታወቅ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የአገሪቱን የተለያዩ አካባቢዎች በመንገድ አውታር በማገናኘት ሥራ ላይ ተጠምዶ አሳልፏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንገድ አውታር ከማገናኘት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በሚያጎለብት ደረጃ ማዘመን ያስፈልጋል በሚል ወደ ‹‹ሰከንድ ጄነሬሽን›› ቅኝት ተሸጋግሯል፡፡

መንገዶች ባለሥልጣን ይህንን እውን ያደረገው ከአዲስ አበባ አዳማ ድረስ የተዘረጋውን ግዙፍ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በመጀመር ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ከ600 ሚሊዮን ዶላር ብድር ነው፡፡ በእስካሁኑ ቆይታ የመንገዱ የሥራ አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱን አንድ የመንገዶች ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በባለሥልጣኑ የታቀደው የሞጆ ሐዋሳ 200 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ ከዚሁ የአዲስ አበባ አዳማ መንገድ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ እውን ሲሆን የአገሪቱን የገቢና የወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ያቀላጥፋል ተብሏል፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ትልቁ የበጀት ተጠቃሚ የሆነው መንገዶች ባለሥልጣን ለ2006 የበጀት ዓመት ከ36 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ ብድርና ዕርዳታን ጨምሮ የተፈቀደለት 28.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር