በሃወሳ ከተማ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ ያለው የማረሚያ ተቋም ግንባታ ከ90 በላይ ተጠናቀቀ

አዋሳ ሐምሌ 19/2005 የደቡብ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በሃዋሳ ከተማ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ ያለው ዘመናዊ የማረሚያ ተቋም ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ገለጸ፡፡ በአስተዳደሩ ማረምና ማነፅ የስራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ኑሪ ሺሾሬ እንደገለጹት የህንጻው መገንባት የህግ ታራሚዎችን በተለያዩ ሙያዎች በማሰልጠን በማረምና በማነፅ የዕውቀትና የክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት በመደበው ገንዘብ የሚካሄደው ግንባታ ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የተለያዩ ሙያ ባለቤት በመሆን አምራችና ብቁ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ማዕከላዊ የማረሚያ ተቋሙ የመመገቢያ አዳራሽ፣የህክምና ክፍል፣የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ቤተመፃሕፍት፣የተለያዩ የሙያ ማስልጠኛ ማዕከል፣ መዝናኛና የስፖርት ሜዳዎችን ያካተተ ሲሆን በሚቀጥለው የበጀት ዓመት አጋማሽ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ መገንባት ታራሚዎች በቆይታቸው በሚያገኙት ዕውቀት በሀገሪቱ በመካሄድ ያሉ የሰላም ፣የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላቸዋል፡፡ ማዕከሉ በክልሉ ለሚገኙ 22 የማረሚያ ተቋማት የሚያገለግል በመሆኑ በህመም ምክንያት ሪፈር የሚፃፍላቸውን ህሙማን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድም ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ከ57 ሚሊዮን ብር በሚበጥ ወጪ በወላይታ ሶዶ፣ በዲላና በሆሳዕና የማረሚያ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ስልጠና ማዕከልና ሌሎችንም በማካተት በአዲስ መልክ የመገንባት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በሚዛን አማንና በበንሳ በተመሳሳይ አዲስ የማረሚያ ተቋማት ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ኮማንደሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር