በሲዳማ ዞን ከ30 ሺህ የሚበልጡ አንቀሳቃሾች ተደራጅተው ወደ ስራ ገቡ

ሃዋሳ ሐምሌ 18/2005 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ30 ሺህ የሚበልጡ አንቀሳቃሾችን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ገለጸ፡፡ ለአንቀሳቃሾቹ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱ ተገልጿል፡፡ በመምሪያው የኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደበበ ተገኝ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የኢንዱስትሪ ልማት መሰረት የሆነውን የአነስተኛና ጥቃቅን መስኮችን የመደገፍና የማብቃት ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት አሰራ ሁለት ወራት 30 ሺህ 673 አንቀሳቃሾችን በተለያየ ማህበራት በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንና ከነዚህም መካከል 8 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ፡፡ መምሪያው አንቀሳቃሾቹ ጥራት ያለውን ምርት አምርተው በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በየደረጃው የክህሎትና የቴክኖሎጂ ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎችን በዞኑ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አዲስ ወደ ስራ የገቡትን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ አንቀሳቃሾች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አንቀሳቃሾቹ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታና በሌሎች ዕድገት ተኮር የስራ ዘርፎች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ በመምሪያው የድጋፍ ማዕቀፎች አፈፃፀምና ክትትል ዋና የስራ ባለቤት ወይዘሮ ሐረገወይን ኃይለሚካኤል በበኩላቸው በዘርፉ ቀደም ብሎ የሚገኙትንና በአዲስ መልክ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ አንቀሳቃሾች ስራቸውን ለመጀመርና ለማስፋፋት ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግር እንዳይገጥማቸው በበጀት ዓመቱ ከ310 ሺህ 990 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ተዘጋጅቶ መሰጠቱን የጠቆሙት ወይዘሮ ሐረገወይን የአንቀሳቃሸችን አቅም በማጎልበት ምርታማ፣ ብቁና በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የአደረጃጀት፣ የተስማሚ ቴክኖሎጂና የመረጃ አገልግሎት ድጋፍና እገዛ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ ለአንቀሳቃሾቹ የገበያ ዕድል ለመፍጠር በተሰራው የተቀናጀ ጥረት 193 ሚሊዮን 983 ሺህ ብር የገበያ ዕድል መፈጠሩንና እስከ አሁን በብድር ከተሰራጨው ገንዘብ ከ60 በመቶ በላይ ለማስመለስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=10158

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር