በሀዋሳ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ተሰራ

አዋሳ ሐምሌ 18/2005 በሀዋሳ ከተማ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ66ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 25 ኪሎ ሜትር መንገድ በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መሰራቱን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡ የማዘጋጃ ቤቱ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስተባበሪ አቶ መብራቴ መለሰ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በበጀት አመቱ መግቢያ ላይ የተጀመረው የድንጋይ ንጣፍ መንገዱ ግንባታ በእቅዱ መሰረት በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልገሎት በቅቷል፡፡ በከተማው አሰተዳደር በጀት የተገነባው የድንጋይ ንጣፉ መንገድ ስራ ሰባት ሜትር ስፋት አለው ብለዋል፡፡ ለእግረኛና ተሽከርካሪ የሚያገልግለው በከተማው ስምንት ክፍለ ከተሞች የተገነባ በመሆኑ በዋጋ ደረጃ ከአስፓልት አንጻር ርካሽና ለረጅም አመታት አገልግሎት እንደሚሰጥ ቢበላሽ በቀላሉ መጠገን የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስራው ሰልጠነው በተደራጁ 148 ድንጋይ ጠራቢና አንጣፊ ማህበር ከስድስት ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው እያንዳንዱ ማህበራት በየቀኑ እስከ 20 ሌሎች ሰዎችን በመቅጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በከተማው የአሁኑን ሳይጨምር ቀደም ብሎ የተሰራ 55 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ እንዳለ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል 17 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ደረጃውን ወደጠበቀ አስፓልት ለማሳደግ በ46 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በግል ተቋራጭ እየተካሄደ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ መብራቴ ይሄው መንገዱ ከነባሩ ቴሌ እሰከ አዴቬንቲስት ቤተክርስቲያን፣ ከመናሃሪያ ዋንዛ ወልደአማኑኤል ዱባለ አደባባይና ከአላሙራ ትምህርት ቤት ወደ ሞኖፓል አቋርጦ የሚያልፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከመንገዱ ስራ እስካሁን ግማሽ ያህሉ መከናወኑንና እሰከ መጪው መስከረም 2006 ተጠናቆ ለአገልገሎት ይበቃል ብለዋል፡፡ ከ26 ሚለዮን ብር በሚበልጥ በጀት በከተማው ከፍተኛ የጎርፍ ተፋሰስ ችግር ያለባቸውን በጥናት በመለየት 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጎርፍ መውረጃና ማሶገጃ እየተሰራ መሆኑም አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በ250 ሚሊዮን ብር አዲስ የአስፓልት መንገድ ለማካሄድ በጨረታ ሂደት ላይ ላይ እንዳለና በቅርቡም ስራውን በመጀመር በአንድ አመት ተኩል ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር