በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በ2006 ዓ.ም የዲግሪና የመሰናዶ መርሃ ግብር የተማሪዎች መግቢያ መቁረጫ ነጥብን ይፋ ሆነ መልካም እድል ለሲዴ ልጆች

አዲስ አበባ ነሐሴ 24/2005 የትምህርት ሚኒስቴር የ2006 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በዲግሪና በመሰናዶ መርሃ ግብር የተማሪዎች መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ዛሬ ይፋ አደረገ። በአዲሱ የትምህርት ዘመን 132 ሺህ 215 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ማግኘታቸውና ከእነዚሁ መካከል ደግሞ 103 ሺሀ 385ቱ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በወጪ መጋራት ማዕቀፍ እንደሚመደቡ ተገልጿል። ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በትምህርት ዘመኑ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በዲግሪ መርሃ ግብር ገብተው ሊማሩ የሚችሉት ተማሪዎች 265 እና ከዛ በላይ ነጥብ ያመጡ ናቸው። ነጥቡ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅን፣ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የሰው ኃይልና የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ ነው የተገለጸው። በዚሁ መሰረት በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስክ ሁሉም መደበኛ ወንድ ተማሪዎች 325 እና ከዛ በላይ ሴቶች ደግሞ 305 እና ከዛ በላይ፣ ለታዳጊ ክልልና ለአርብቶ አደር ልጆች ወንዶች 305 እና ከዛ በላይ ሴቶች 300 እና ከዛ በላይ ያመጡ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ይደለደላሉ። በተመሳሳይ የግል ተፈታኝ የሆኑ ወንዶች 330 እና ከዛ በላይ ሴቶች 320 እና ከዛ በላይ ካመጡ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ይደለደላሉ እንደሚደለደሉ ተገልጿል። በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስክ መደበኛ ተማሪዎች ወንዶች 285 እና ከዛ በላይ ሴቶች 280 እና ከዛ በላይ፣ ለታዳጊ ክልልና ለአርብቶ አደር ልጆች ወንዶች 275 እና ከዛ በላይ ሴቶች 270 እና ከዛ በላይ ነጥብ ያመጡ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚደለደሉ ታውቋል። ለሁሉም መስማት የተሳናቸው 270 እና ከዛ በላይ፣ ማየት የተሳናቸው 230 እና ከዛ በላይ እንዲሁም ሁሉም የግል ተፈታኞች 290 እና ከዛ በላይ መሆኑ ተመልክቷል። በትምህርት ዘመኑ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ ተማሪዎች 70 በመቶዎቹ በተፈጥሮ ሳይንስና ኢንጅነሪንግ፣ 30 በመቶዎቹ ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስ መስክ እንደሚመደቡ ለማወቅ ተችሏል። በተፈጥሮ ሳይንስና ኢንጅነሪንግ ከሚመደቡት መካከልም 40 ነጥብ 02 በመቶ የሚሆኑት በኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ የሚገቡ ይሆናል። በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የመግባት ዕድል ያገኙና ነገር ግን በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች በፍላጎታቸው መሰረት መማር እንደሚችሉም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ማለፊያ ነጥብ አግኝተው በመንግሥት ዩኒቨርሲቲ መመደብ ያልቻሉ ተማሪዎች በግል ዩኒቨርሲቲዎች በተለዩ መርሃ ግብሮች መማር እንደሚችሉም አመልክቷል። የማለፊያ መቁረጫ ነጥብ ያላገኙ ተማሪዎች ራሳቸውን አዘጋጅተው በ2006 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በግል ተመዝግበው ሊፈተኑ እንደሚችሉ ሆኖም በአንድ ሰርቴፊኬት የተገኘው ውጤት ብቻ እንደሚሰላ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በተመሳሳይ በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሰርተፊኬት ፈተና የወሰዱ የሁሉም ክልሎች የመደበኛና የማታ ተማሪዎች የመሰናዶ መርሃ ግብር መግቢያ ነጥብ ለወንዶች 2 ነጥብ 71 እና ከዛ በላይ ለሴቶች 2 ነጥብ 29 እና ከዛ በላይ ሆኗል። ማየትና መስማት ለተሳናቸውና ልዩ ፍላጎት ላላቸው የመሰናዶ መርሃ ግብር መግቢያ ነጥብ 2 ነጥብ 14 እና ከዛ በላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ልዩ ድጋፍ በሚደረግላቸው ታዳጊ ክልሎች ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሆነው በዚያው ለተፈተኑ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለዩ ዞኖችና ወረዳዎች ለሚኖሩ የአርብቶ አደር ልጆች ለወንዶች 2 ነጥብ 29 እና ከዛ በላይ ለሴቶች 2 ነጥብ 14 እና ከዛ በላይ እንደሆነ ተገልጿል። ፈተናውን በግል ከወሰዱ ተፈታኞች መካከልም 2 ነጥብ 86 እና ከዛ በላይ ያስመዘገቡ ወንዶች እንዲሁም 2 ነጥብ 29 እና ከዛ በላይ ያስመዘገቡ ሴቶች በመደበኛ መሰናዶ መርሃ ግብር እንዲማሩ ይደረጋል። የግል ተፈታኞቹ ውጤት በ2005 ዓ.ም የአንድ ሰርተፊኬት ውጤት የሚሰላ ሆኖ እንግሊዝኛና ሂሳብን ጨምሮ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡባቸው ሌሎች አምስት የትምህርት ዓይነቶች ውጤት ተደምሮ ለሰባት በማካፈል እንደሆነም ተብራርቷል። የመሰናዶ መርሃ ግብር ምደባው 70 በመቶ በተፈጥሮ ሳይንስና 30 በመቶ ደግሞ በማኅበራዊ ሳይንስ መስክ እንደሆነም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=11401&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር