በሲዳማ ዞን በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለተደራጁ አባላት ከ193 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጠረ

አዋሳ ነሐሴ 1/2005 በሲዳማ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለተደራጁ ከ30 ሺህ በላይ አባላት ከ193 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ገለጸ፡፡ በመምሪያው የኢንተርፕራይዝ ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደበበ ተገኝ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የገበያ ትስስሩ የተፈጠረው ማህበራት ሰፊና ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር እንዲኖራቸውና ምርትና አገልግሎታቸውን በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ነው፡፡ አባላቱ ከተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች መካከል ማንፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ምግብ ማቀነባበር፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ንግድ፣ የከተማ ግብርና፣ ኮብል ድንጋይ ማንጠፍ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የገበያ ትስስር የተፈጠረው በዞኑ ባሉት ሁለት የከተማ አስተዳደሮችና 19 ወረዳዎች መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዞኑ 30 ሺህ 620 አባላት በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የማህበሩ አባላትም ከ14 ነጥብ5 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ መቆጠባቸውን ጠቁመዋል፡፡ ማህበራት በተደራጁበት የስራ ዘርፍ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የምክር፣ የንግድ ስራ አመራር ስልጠናና ሌሎችም ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአዲሱ ስትራቴጂ ማዕቀፍ መሰረት አዲስ ማህበራት ለመበደር ከሚፈልጉት ገንዘብ ውስጥ 20 በመቶ መቆጠብ እንዳለባቸው መመሪያ የተቀመጠ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 13 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ለሚገኙ ማህበራት በዞኑ ከሚገኙ አምስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ የተስማሚ ቴክኖሎጂ አቅርቦት መደረጉን የጠቀሱት የስራ ሂደት አስተባባሪ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በተመለከተም ከ300 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡ ከማህበሩ አባላት መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት በተፈጠረላቸው የስራ ዕድልና የገበያ ትስስር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=10601

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር