ከሐዋሳ እስከ ሞጆ ለሚገባው የኤክስፕረስ መንገድ ከደቡብ ኮሪያ ብድር ተገኘ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2005(ዋኢማ) - ኢትዮጵያ ከሐዋሳ ወደ ሞጆ ለሚወስደው ፈጣን (ኤክሰፕረስ)መንገድ ግንባታ ከደቡብ ኮሪያ የጠየቀችውን 700 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአፋጣኝ እንዲለቀቅ የአገሪቱ ፓርላማው አፈ ጉባዔ ግፊት እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠየቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ካንግ ቻንግ ሂ የተመራውን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንዳሉት በሁለቱ አገሮች መካከል በደም የተሳሰረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በኢኮኖሚና በንግድ መስኮችም ማጠናከር አስፈላጊ ነው። 

ደቡብ ኮሪያ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል ረገድ ያላትን ሰፊ አቅም በመጠቀም በቴክኖሎጂና በዕውቀት ሽግግር ለኢትዮጵያ የሚቻላትን ትብብር እንድታደርግ ጠይቀዋል። አቶ ኃይለማርያም ከሐዋሳ ወደ ሞጆ ለሚወስደው ፈጣን መንገድ ወይም ኤክሰፕረስ መንገድ ግንባታና የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ የጠየቀችው ገንዘብ በፍጥነት እንዲለቀቅ የፓርላማው አፈ ጉባዔ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

ከደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ብድር አነስተኛ ወለድና በረዥም ጊዜ የሚከፈልበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ የአገሪቱ ፓርላማ የግፊትና የማግባባት ጥረት እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ ኃይለማርያም የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ፓርክ ጊሁን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ኦሽንያ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አረጋ ኃይሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ካንግ ቻንግ ሂ በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች ምክር ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት፣የአገሮቹ የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር የበለጠ እንዲሻሻልና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር የመንግስታቸው ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል። 

ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የላቀ ግምት እንደምትሰጠው የተናገሩት አፈ ጉባዔው፣ የአገራቸው ባለሃብቶች በቆዳ፣በጨርቃጨረቅ፣በኤሌክትሮኒክስና በሌሎችም መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ግፊት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። 

በሁለቱ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

አገራቸው በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለኢትዮጵያ ልምዷን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሴዑል በረራ እያደረገ በመሆኑ ደቡብ ኮሪያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል። 

እንደ ኢዜአ ዘገባ አፈ-ጉባኤ ካንግ ቻንግ ሂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደቡብ ኮሪያን እንዲጎበኙ ያቀረቡት ግበዣም ተቀባይነት ማግኘቱን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። 
http://www.waltainfo.com/index.php/2011-09-07-11-53-43/9166-2013-07-11-20-46-43

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር