በደቡብ ክልል የፕሬዚዳንትነትን ቦታ ለሲዳማ ብሄር ተወላጆች ክፍት በማድረግ ኢህኣዴግ የሲዳማን ክልል ጥያቄ በማፈን ላይ ነው

ሲዳማ ባለፉት 20 ኣመታት ህዝባዊ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በተመለከተ ፖለቲካዊ ኣንድነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያሳየው የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንትነትን ቦታ በሌላው የደቡብ ብሄር በተነጠቀበት ወቅት ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ይሄውም የቀደሞውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ኣቶ ኣባተ ኪሾን በሙሲና ተከሰው ከስልጣን ላይ መነሳታቸውን ተከትሎ ወደ ክልሉ ፕሬዚዳንትነት የመጡት የኣሁን የኣገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ብቻ ነው፤ ሲዳማ ህዝቡም ሆነ ህዝቡ የመረጣቸው የፖለቲካ መሪዎች በኣንድ ኣፍ የተናገሩት እና ለሁሉም ጥቅም መከበር ኣብረው የሰሩት።

ከጊዜ ውጭ በተለይ የሲዳማ ተወላጆች የክልሉን ፕሬዚዳንትነትን በያዟቸው ወቅቶች በሙሉ ማለት ይቻላል በሲዳማ ህዝብ ጥቅሞች ላይ ኣንድ ኣይነት ኣቋም ተይዞ ኣልታየም። በተለይ የሲዳማን የክልል ጥያቄን በተመለከት የህዝቡ ፍላጎት እና የፖለቲካ ኣመራሮቹ ፍላጎት ለየቅል ሆነው ታይተዋል። ለኣብነት ያህል ኣቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ በወቅቱ የሲዳማ ዞን ዋና ኣስተዳዳሪ በነበሩት በኣቶ ገርመው ጋርጄ የምመራው የሲዳማ የፖለቲካ ኣመራር ለሲዳማ የክልል መንግስት ያስፈልገዋል በማለት ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ ካድሬዎቹን በማሰማራት ህዝብ የማሳመን ስራ ስርቷል። የክልል ጥያቄ በህዝብ ውስጥ ስር እንዲሰድ እና በኣንድነት ሆ! ብሎ እንድደግፋቸው ኣድርገዋል። በጊዜ የሲዳማ ህዝብም በኣመራሮች ለህዝባቸው መቆርቆር ከመደሰቱ እና ከመኩራቱ በላይ ለጥያቄው መሳካት በነብሱን ገብረውለታል። ይህ ጊዜ የሲዳማ ኣባቶች እና እናቶች በልጆቻቸው የኮሩበት፤ ምራቃቸውን ተፍተው የመረቋቸው ጊዜ እንደነበር የምታወስ ነው።

በእርግጥም በወቅቱ በያዙት እና በፈጸሙት ጀግንነት መላው ለህዝብ መብት ተሞጋች ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኣድንቋቸዋል። ህዝብን የማሳመን ስራ መስራቱ ብቻ ሳይሆን በዞኑ ምክር ቤትን የክልል ጥያቄው ህገ መንግስታዊ መንገድ ተከትሎ እንድሰጥ በሙሉ ድምጽ እንድጠይቅ ማድረጋቸው ለኣገሪቱ ህገ መንግስት መከበር ያላቸውን የማያወላዳ ኣቋም እንድያንጸባርቁ ማድረጉ ይታወሳል።

ታዲያ ያን ጊዜ ለሲዳማ ህዝብ የክልል መንግስት ወይም የሲዳማ ክልል ይገባል በማለት ለሲዳማ ህዝብ ጥቅም እና መብት የታገሉለት የፖለቲካ መሪዎቹ መቶ በመቶ ድጋፍ ያነሱት የክልል ጥያቄ ከጥቅት ጊዜ በኃላ መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ ማንሳታቸው ህዝቡን ኣሳዝኗል።

ኣመራሮቹ ለህዝቡ ጥያቄ ያሳዩትን ድጋፍ በራሳቸው ጊዜ መንፍጋቸው ከበስተኃላው ምን ነበረው ተብሎ ስጠየቅ ምላሽ የምሆነው፤በወቅቱ የህዝቡን ጥያቄ ያራግቡ የነበሩት ኣመራሮች በስልጣን መደለላቸውን መገንዘብ ኣያዳግትም። ለምሳሌ ያህል በወቅቱ ቀንደኛ የሲዳማ ክልል ጠያቅ የነበረው የዞኑ ዋና ኣስተዳደር ኣቶ ገረመው ጋርጄ በሚኒስትር ዴኢታ ማዕረግ ወደ ፌደራል መንግስት መሄድ እና ሌላኛው የክልል ጥያቄ በተለይ መጀመሪያ ላይ በመደገፉ የምታወቀው ኣቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወደ ክልል ፕሬዚዳንትነት መምጣትን ለኣብነት ማንሳት ይቻላል።

የእነዚህ ቀንደኛ የሲዳማ መሪዎች የኣቋም ለውጥ ማድረግ ለሲዳማ የክልል ጥያቄ እስከ ኣሁን ድረሳ ምላሽ ማጣት እንዴ ምክንያትነት ማንሳት ይቻላል።ድርጊቱም የኣገሪቱ ገዥው ፓርቲ ኢህኣዴግ በሲዳማ ላይ የምከተለውን የፖለቲካ ስልት በግልጽ ያሳየ ሆኗል። ይህም ማለት ለሲዳማ ህዝብ ጥቅም እና ጥያቄዎች ምላሽ የሚታገሉ የሲዳማን ልጆች በተለያዩ ስልጣንን በመሳሰሉ ጥቅማ ጥቅሞች ማታለል ብሎም የተለያዩ የፈጠራ ስሞችን እና ባህር በመስጠት የማሰር እና ለህዝብ ኣገልጋይነት ያላቸውን ተነሳሳሽነት የመምታት ስራ ነው።

የእነዚህ የሲዳማ የፖለቲካ መሪዎች በተለዩ ጥቅማጥቅሞች ተደልለው የኣቋም ለውጥ ማድረግ በመላው ዞን ውስጥ ተመሳሳይ ኣቋም እንዳይያዝ ኣድርጓል። የሲዳማ ኣመራሮች እርስበርሳቸው እንድከፋፈሉ ሆኗል። ለዚህም ማሳያ በዚህ ኣመት መጀመሪያ ላይ ኣንድ ኣቋም ለመያዝ እንድያስችላቸው ከወረዳ ኣመራሮች ኣንስቶ እስከ ፈዴራል ድረስ ያሉት የሲዳማ ኣመራሮች በሃዋሳ ከተማ ከትመው መገማገማቸው እና የክልል ጥያቄውን እንዳይቀበሉ መደረጋቸው የምታወሰ ነው።

ይህም የምያሳየው ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደምባለው፤ ያኔ የደርግ ስርኣት የሲዳማን ነጻ ኣውጪ ኃይል በወታደራዊ ኣቋሙ መቋቋም ሲያቅተው የራሱን የሲዳማ ህዝብ ልጆች ኣሰልጥኖና ኣስታጥቅ በሲዳማ ነጻ ኣውጪዎች ላይ እንዳዘመተው እና የሲዳማን የነጻነት ትግል እንደገታው ሁሉ ዛሬ ደግሞ ኢህኣዴግ የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ላለመመለስ የራሱ ልጆች በስልጣን እና በሌሎች ጥቅማጥቅሞች በማባበል በገዛ ህዝባቸው ላይ የተለየ ኣቋም እንድይዙ በማድረግ ላይ ነው።
ለዚህም የደቡብ ክልል የፕሬዚዳንትነትን ቦታ ለሲዳማ ተወላጆች ክፍት በማድረግ የሲዳማ የክልል ጥያቄ የማፈን ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።

ከላይ እንዳነሳሁት ላለፉት ስምንት ኣመታት የደቡብ ክልል ኣንቀጥቅጦ የገዙት እና የሲዳማን ክልል ጥያቄ ወቅቱን ያልጠበቀ በምል ሲያጣጥሉ የነበሩት ኣቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለኢህኣዴግ ለዋሉለት ውለታ በፌደራል መንግስት ቦታ ያገኙ ሲሆን በእርሳቸው ቦታ ኣቶ ደሴ ዳልኬ ተተክተዋል።

ኣቶ ደሴ ዳልኬ ባለፉት ኣስራ ሁለት ኣመታት በሲዳማ ዞን ውስጥ በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች ላይ የሰሩ እና ላለፉት ሶስት ዓመታት የሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው የቆዩ ናቸው።

የኣቶ ደሴ ዳልኬ ወደ ደቡብ ክልል ተመልሰው መምጣት ለሲዳማ ያለው እድምታ ምን እንደሆነ ለጊዜው ግልጽ ባይሆንም በሲዳማ ዘንድ የተደበላለው ስሜት ፈጥሯል። ኣቶ ደሴ ዳልኬ በሲዳማ ህዝብ ዘንድ በየጊዜው እየተነሳ የቆየውን የሲዳማ ክልል ጥያቄን በተመለከተ የሚኖራቸውን ኣቋም ከዚህ በፊት ከነበሩት የክልሉ መሪዎች የተለየ እንደማይሆን የተገመተ ሲሆን ለክልል ጥያቄው ኣዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርጉ ከሆነ የሲዳማ ህዝብ ድጋፊ እና ፍቅር ሊያገኑ ይችላሉ ተብሏል። ነገር ግን የተለየ ኣቋም ይኖራቸው ይሁን? ቆይተን የምናየው ይሆናል።


ኖሞናኖቶ ነኝ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር