በሀዋሳ ከተማ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጠ

አዋሳ ሐምሌ 10/2005 በሀዋሳ ከተማ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ523 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 56 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ለመግባት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ገለጸ፡፡ በከተማው የዘንድሮን ሳይጨምር 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው ሌሎች ባለሀብቶች በፈጠሯቸው የስራ እድሎች ከ28ሺህ 600 ለሚበልጡ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡ በመምሪያው የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠት ፐርፎርመርና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወግደረስ ወንድሙ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከ523 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ፍቃድ የወሰዱት 56 ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፣ በኮንስትራከሽን ፣በሆቴልና ሌሎች ማህበራዊ አገልገሎቶች ለመሰማራት ነው፡፡ ባለሀብቶቹ በግላቸው ባላቸውና በጊዜዊነት በተሰጣቸው ቦታዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውና ስራ የጀመሩ እንዳሉ አመልክተው በሙሉ አቅማቸው ሲንቀሳቀሱ 2ሺህ ሰዎች የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለኢንቨስትመንት ልማት የሚውል 420 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ዘንድሮ በጥናት ተለይቶ ለአልሚ ባለሀብቶች መዘጋጀቱንና ከዚሀም ውስጥ 270 ሄክታር በሀገር አቅፍ ደረጃ በማዕከላዊ መንግስት ለአንዱስትሪ ልማት የሚፈለግ ነው ብለዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኢንዱስትሪ ልማት ከተመረጡ አምስት ከተሞች መካከል ሀዋሳ አንዷ በመሆኗ ማዕከላዊ መንግስት ከውጪና ከሀገር ውስጥ ለሚጋብዛቸው አልሚ ባለሃብቶች እንዲውል ያዘጋጁት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቀሪው 150 ሄክታር መሬት በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣በሪል ስቴትና በአገልግሎት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች እየዋለ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ በከተማው ከ1997 ጀምሮ እስካሁን 9ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከወሰዱ 1ሺህ 716 ባለሀብቶች መካከል 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው 519 ባለሀብቶች ወደ ስራ በመግባት በመፈጠሯቸው የስራ ዕድሎች ከ28ሺህ 600 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡ ባለሃብቶች የተሰማሩባቸው የስራ መስኮች በከተማ ግብርና፣ በኢንዱስትሪና በማህበራዊ አገልገሎቶች ላይ ነው ብለዋል፡፡ ሁሉም ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው መንቀሳቀስ ሲጀምሩም ከ103ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማና አካባቢ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅመማ ቅመም፣ የቡና ማቀነባበሪያ ፣የሆቴልና ቱሪዝም፣ የመዝናኛ ጀልባ ግንባታን ጨምሮ ገና ያልተነኩ ሌሎች ዘርፈ አማራጮች በጥናት መለየታቸውን ጠቁመው መስሪያ ቤታቸው እንዚህን አማራጮችና ማበረታቻዎችን በመገናኛ ዘዴ በማስተዋወቁ የባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይነት ለሚመጡ ባለሀብቶች ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ከተማው ከአዲስ አበባ በቅርበት የሚገኝ በመሰረተ ልማትና በሌሎች አገልግሎቶች የተመቻቸ ሁኔታ እንዳለ በመረዳት ማንኛውም ባለሀብት በሚፈልገው ዘርፍ ቢሰማራ ራሱን ጠቅሞ የከተማውን ዕድገት ለማፈጣንና የስራ ዕድሎችን ለማስፋፋት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=9800&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር