በደቡብ ክልል በተጠነቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የልማት መስኮች የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል

አዋሳ ሐምሌ 06/2005 በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት በሁሉም የልማት መስኮች መላውን የክልሉን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረጉ አበረታታች ስራዎች መከናወናቸውን የትምህርት ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለክልሉ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት አመት በግብርና በትምህርት በጤና በመንገድ በንግድ ኢንዱስትሪ፣በከተማ ልማትና ሌሎች መስኮች የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማና መላውን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው። በግብርናው መስክ አርሶ አደሩ መስኖ ተጠቅሞ በበጋ ወራት በገበያ ተፈላጊ የሆኑና የተሻለ ዋጋ የሚያስገኙ ሰብሎችን እንዲያመርት እንዲሁም የራሱንና የቤተሰቡን ጉልበት በአግባቡ ልማት ላይ በማዋል ገቢውን እንዲያስድግ በተሰራ ስራ አበረታች ውጤት ከመመዝገቡ በተጨማሪ በአከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት ወቅቱ፣ ስርጭቱና መጠኑ እየተዛባ ካለው የዝናብ ተፅዕኖ የሚያላቅቁ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡ በአነስተኛ ወጪና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሁለት ዙር የመስኖ ልማት 180ሺህ 905 ሄክታር መሬት በስራስር፣ ቦሎቄ፣ ቦቆሎ፣ እና የጓሮ አትክልቶች በመሸፈን 26 ሚሊዮን 606ሺህ 342 ኩንታል ምርት ማምረት መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ከክልሉ የሚመረተውን ቡና ጥራትና ደረጃ በማስጠበቅ በብዛት አምርቶ ለውጪ ገበያ በማቅረብ ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሪ ለማሳደግና አምራች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን 42 ሺህ 189 ቶን የታጠበና 40ሺህ 952 ቶን ያልታጠበ ቡና በግልና በማህበረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል። በክልሉ በከተማና ገጠር 704 የውሃ ተቋማትን በመገንባት፣የማስፋፊያና የጥገና ስራ በማከናወን 1 ሚሊዮን 195ሺህ 557 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸው የክልሉን የመጠጥ ውሃ ሽፋን በገጠር 54 ነጥብ 6 በከተማ 79 ነጥብ 4 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል። አርብቶ አደሩ ከክብት እርባታ በተጨማሪ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ በግብርና ስራ እንዲሰማራ 9 ሺህ 048 አርብቶ አደር አባወራና እማወራዎችን በመንደር ለማሰባሰብ ታቅዶ 2ሺህ 600 ሄክታር ቦታ በማዘጋጀት እስካሁን 4ሺህ 129 የቤተሰብ ኃላፊዎች መሰባሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሚሰበሰብ ገቢን ለማሳደግ እስከታችኛው መዋቅር ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ በመቻሉ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለ ጠቁመዋል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የወጣውን የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ ተግባራዊ ለማድረግ በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ትኩረት በመስጠት በየትምህርት ቤቱ የቤተ ሙከራ አገልግሎት እንዲስፋፋና ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር የማሰደገፍ ስራ መሰራቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል። በሚሊኒየሙ ዕቅድ መሰረት የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት በመደበው 302 ሚሊዮን 997 ሺህ 223ብር 50 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ ሁሉንም ቀበሌዎች እርስ በእርስና ከዋናው መንገዶች ጋር በማገናኘት አርሶና አርብቶ አደሩ ያመረታቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ከ6ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የቀበሌ ተደራሽ መንገድ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል። በሁለም የልማት መስኮች የተመዘገቡት ውጤቶች አጥጋቢ ቢሆኑም ገና በርካታ ስራዎች ስላሉ በተገኘው ውጤት ብዙም ባለመዘናጋት ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኬት በተለይ የምክር ቤቱ አባላት ጠንክሮ መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የክልሉ መንግስት የ2005 በጀት ዓመት ሪፖርት ላይ በመወያየት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር