የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብርን ለመከታተል ስድስት ባለሥልጣናት ኃላፊነት ወሰዱ

የዜጐችን የሰብዓዊ መብት ለማስከበር መንግሥት ነድፎታል የተባለውን የሦስት ዓመታት የድርጊት መርሐ ግብር በበላይነት የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ ተመሠረተ፡፡ ስድስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የኮሚቴው አባል በመሆን ኃላፊነት ወስደዋል፡፡
የድርጊት መርሐ ግብሩን በበላይነት ለመከታተል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ በመሆን የተመረጡ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ነጋ ፀጋዬ በምክትል ሰብሳቢነት ተመርጠዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የብሔራዊ ኮሚቴው ጸሐፊ ሆነዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው የኮሚቴው አባላት ሆነው የመከታተል ኃላፊነቱን ወስደዋል፡፡ 
ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር በሚል ስያሜ መንግሥት ያዘጋጀው ሰነድ በሦስት ዓመታት ውስጥ የዜጐችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ በማክበርና በማስከበር፣ በዚህ ረገድ የሚታይበትን ከፍተኛ ጉድለት ለመቅረፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 
በቅርቡ በፓርላማ የፀደቀው የድርጊት መርሐ ግብር ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል የሕግ አስከባሪዎች ያላግባብ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚፈጽሙት ድብደባ አንዱ ሲሆን፣ እንደዚህ ዓይነት ተግባር በሚፈጽሙ የፖሊስ አባላት ላይ ጥብቅ የሆነ ዕርምጃ ለመውሰድ በዕቅዱ ተካቷል፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በእስር በመያዝ ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ምርመራ ማድረግ በሕግ አስከባሪው ዘንድ የሚታይ ጉድለት መሆኑን በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ለማድረግ የጊዜ ገደብ መውጣት ስላለበት፣ ይህም በዜጐች መብት ላይ የሚፈጸም በደልን ያስቀራል የሚል ዕቅድ በድርጊት መርሐ ግብሩ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመተግበር የታቀዱ ናቸው፡፡ 
በተጨማሪም የዜጐችን የመኖር፣ መጠለያ የማግኘት፣ የሕፃናትን መብትና ሌሎች መሠረታዊ መብቶችን በተሻለ ማስከበር የድርጊት መርሐ ግብሩ ዓላማዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር