‹‹ኔትዎርክ የለም››

ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ የአገሪቱ ባንኮች በግልና በኅብረት ሆነው እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ስድስት የግል ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ከዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች አንዱ በመሆን የሚጠቀሰው የኤቲኤም እዚህ እንደ አዲስ እንየው እንጂ በዓለም ላይ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ40 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡
ሌሎች ዘመናዊ የምንላቸውን የባንክ የአገልግሎት ዓይነቶችም ገና በመግባት ላይ ናቸው ወይም ለማስገባት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ለአገራችን አዳዲስ የምንላቸውን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ለማግኘት ባንኮች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ቅርንጫፎቻቸውን በኔትዎርክ አስተሳስረዋል፡፡ በሞባይል ገንዘብ ለማዘዋወር የሚያስችለውን ቴክኖሎጂም ሊጀምሩ ነው፡፡ ከኤቲኤም ጀምሮ ወደፊት ተግባራዊ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ወደተግባር ለመለወጥ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የቴሌን ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ አገልግሎቶቹ ከኔትዎርክ ጋር የሚያያዙ በመሆኑ የኔትዎርክ ችግር ካለ አገልግሎቱን መስጠት አይችልም፡፡ ሰሞኑን እንደታዘብነው ግን የኔትዎርክ ችግር በትንሽ ደረጃ የተጀመረውን ዘመናዊ የባንክ ሥራ እየፈተነው ነው፡፡
በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው በሚባለው የኔትዎርክ ችግር የባንክ ደንበኞች ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም በማለት እያማረሩ ናቸው፡፡ ገንዘብ ለማስገባትና ለማስወጣት ብዙ እንግልት እየደረሰብን ነው የሚሉት የባንክ ደንበኞች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ በተደጋጋሚ መከሰቱን ይጠቁማሉ፡፡ 
ሰሞኑን በኔትዎርክ ችግር ምክንያት እየተጉላላን ነው ካሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች መካከል የአንድ ድርጅት ሠራተኛ ጨርቆስ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስገባት የነበረባቸውን ከ400 ሺሕ ብር በላይ ለማስገባት ያለመቻላቸውን በምሬት ሲናገሩ አድምጫለሁ፡፡ 
እህ ብዬ ያዳመጥኳቸው እኚህ ሠራተኛ እንደገለጹልኝ፣ በድርጅታቸው አሠራር መሠረት ይህንን ያህል ገንዘብ ባንክ ሳይገባ በካዝና ማስቀመጥ ወይም በእጅ መያዝ አይፈቀድም፡፡ ሆኖም ባለፈው ሳምንት ኔትዎርክ የለም በሚል ወደ ባንክ መግባት የነበረበትን ገንዘብ ማስገባት አልቻሉም፡፡ በኔትዎርክ ችግር ምክንያት የባንክ ደንበኞች ገንዘብ ለማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ለማውጣትና ለማንቀሳቀስም እየተቸገሩ ነው፡፡  
የኤቲኤም ተጠቃሚዎችም ገንዘብ ለማውጣት ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ባንኮች በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ዕርምጃ በጀመሩበት በዚህ ወቅት ኔትዎርክ በሌለ ቁጥር አገልግሎት የሚቋረጥ መሆኑን ባንኮቹም ይገልጻሉ፡፡ 
ኔትዎርክ የለም፣ መብራት ተቋርጧል በሚል የሚፈጠረውን የደንበኞች መጉላላት ለማስቀረት ባንኮቹ የራሳቸውን የተለየ አሠራር መቀየስ ግድ እንደሚላቸው እያመለከተ ነው፡፡ 
የጠራ የኔትዎርክ አለመኖር በባንኮች ላይ ብቻ ሳይሆን የሞባይልና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ የሚፈጥረውም ችግር ቀላል አለመሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሆኖም እንደባንክ ያሉ የአገልግሎት ተቋማት በኔትዎርክ ችግር ደንበኞችን ማስተናገድ ያለመቻላቸው የበለጠ አሳሳቢ ይሆናል፡፡ 
ችግሩ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆን ወይም አልፎ አልፎ ሊከሰት የሚችል ቢሆን እንኳን ደንበኞች እየተቸገሩም ቢሆን ነገሩን ችላ ሊሉት ይችላሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ባለፈው ሳምንት በአንዳንድ የባንክ ቅርንጫፎች ለሁለትና ሦስት ቀናት ኔትዎርክ የለንም በሚል የተፈጠረውን ዓይነት መጉላላት ግን ደንበኞች ሊቀበሉት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ በቀድሞው አሠራር ልንስተናገድ ይገባል የሚል እምነት ስላላቸው ነው፡፡ 
ከዚህ ኔትዎርክ የለም ከሚል ችግር ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ነው በሚባለው ችግር ዙሪያ ስንጨዋወት፣ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ገጠመኝ ያለው ክስተት አስገርሞኛል፡፡ ባልደረባዬ ሲም ካርድ ይጠፋበትና የጠፋበትን ሲም ካርድ ለመተካት ልደታ አካባቢ ወዳለ የቴሌ ቅርንጫፍ ይሄዳል፡፡ አንድ ደንበኛ ሲም ካርድ ለማውጣት የሚፈጀው ጊዜ የተወሰኑ ደቂቃዎች በመሆኑ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ቴሌ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሲሄድ ግን እንዳሰበው ሊስተናገድ አልቻለም፡፡ የተሰጠው መልስ ኔትዎርክ ስለሌለ የጠፋበትን ሲም ካርድ ማግኘት የማይችል መሆኑን ነው፡፡
ይህንን ገጠመኙን ሲያጫውተኝ በቴሌም ቅጥር ግቢ የኔትዎርክ ችግር አለ እንዴ? የሚለው ጥያቄውም ፈገግ አድርጐኝ ነበር፡፡ የባልደረባዬ ገጠመኝ በዚህ ብቻ የሚያቆም አይደለም፡፡ በልደታ የቴሌ ቅርንጫፍ ማግኘት ያልቻለውን አገልግሎት ከሌላ ቅርንጫፍ አገኛለሁ በሚል አየር ጤና አካባቢ ወደሚገኘው የቴሌ ቅርንጫፍ ሲሄድ ተመሳሳይ የሆነ መልስ ይሰጠዋል፡፡ ‹‹ኔትዎርክ የለም››
ከዚህ አንፃር ዘመናዊ አሠራሮች እየተስፋፉ የዜጐች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ሥራ ከቴሌ አገልግሎት ጋር እየተሳሰረ ባለበት ወቅት፣ ኔትዎርኩን አስተካክልልን የምንለው ቴሌ ሳይቀር ‹‹ኔትዎርክ የለም›› በሚል አገልግሎት ለመስጠት ያለመቻሉን ነው፡፡
እርግጥ ችግሩ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ነው ቢባልም የኔትዎርክ ችግር አሁንም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ እንደባንክ ያሉ ተቋማት ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የጀመሩት እንቅስቃሴ እንዲህ ባለው ችግር የሚተጓጐል ከሆነ ወደፊት ሙሉ ለሙሉ የቴሌ አገልግሎት ለሰኮንድ እንዳይጓደል የሚፈልጉ አገልግሎቶች ሲመጀመሩ እንዴት ሊኮን ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ለነገ የማይባሉ የገንዘብ ዝውውሮች እንዴት ሊስተናገዱ ነው፡፡ በሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር ሲጀመር ቴሌ እንዲህ ዓይነቱን ክፍተት እንዴት ለመድፈን እንዳሰበ ባናውቅም፣ የወደፊቱን ትተን አሁን ባለው ደረጃ በኔትዎርክ ችግር ለሚስተጓጐሉ እንቅስቃሴዎች ፈጣን ምላሽ እንዳለበት ማስታወሱ መልካም ነው፡፡ በተለይ ባንኮች የኔትዎርክ ችግር ሳቢያ አገልግሎታቸውን ፈልገው የሚመጡ ደንበኞችን በኔትዎርክ እያሳበቡ ጊዜ ከሚፈጁ፣ ችግሩ የጠራ እስከሚሆን ድረስ በተመለመደው አሠራር ጭምር ደንበኞችን ሊያስተናግዱ ይገባል፡፡ 
አያድርስና የኔትዎርክ ችግሩ ከቀናት አልፎ ሳምንታትን ቢያስቆጥር ኔትዎርክ እስኪመጣ አገልግሎት አይሰጥም አይባልም፡፡ ባንኮቻችን ኔትዎርክ ሳይኖርም አገልግሎት ይጡ፡፡ ቴሌም የቤት ሥራውን ይሥራ፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር