ሃዋሳን ጨምሮ የከተሞች ማስፋፍያ እና የኢኮኖሚ እድገት መርሀ ግብር ተግባራዊ ሊሆን ነው

የከተሞች የተቀናጀ ማስፋፍያ እና የልማት መርሀ ግብርን ተግባራዊ ማድረግ በከተሞች አያደገ ለመጣው የመሬት አቅርቦት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የከተሞች ማስፋፍያ እና አካባቢ ልማት መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው፡፡
የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ሞክርያ ሀይሌ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በከተሞች መሰረተ ልማት፣ እድገት እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ስትራቴጂ ተግባራዊ ተደርጎ በከተሞቹ የማስፈፀም አቅምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ውጤት የተገኘ ቢሆንም የተቀናጀ የከተሞች ማስፋፋትና የልማት ፕሮግራምን ውጤታማ ከማድረግ አንፃር ግን ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
አሁን በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ አድራጊነት በሙከራ ደረጃ በአራት ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሚደረገው የከተሞች ማስፋፊያ እና አከባቢ ልማት መርሀ ግብር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡
መርሀ ግብሩ በፈጣን የከተሞች መስፋፋት እና የኢኮኖሚ እድገት ሳቢያ እያደገ ለመጣው የቤቶችና ኢንዱስትሪ ግንባታዎች የመሬት አቅርቦት እንዲኖር ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ የከተሞችን ገቢ በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
መርሀ ግብሩ በሙከራ ደረጃ በአዳማ፣ ሀዋሳ፣ ባሀርዳር እና መቀሌ ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በመጪው ጥር ወር ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ፅሕፈት ቤት ዘግቧል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር