የቡና ቦርድ በድጋሚ ሊቋቋም ነው

መንግሥት ከዓመታት ቆይታ በኋላ በድጋሚ የቡና ቦርድ ለማቋቋም ወሰነ፡፡ በአሁኑ ወቅት የቡና ዘርፍ ራሱን የቻለ ባለቤት ስለሌለው ችግር ውስጥ ገብቷል በሚል ምክንያት በድጋሚ የቡና ቦርድ እንዲቋቋም መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
እስካሁን መንግሥት ስትራቴጂ የሚላቸውን ዘርፎች የሚከታተል፣ ችግራቸውን የሚፈታና የሚቆጣጠር ኤጀንሲ ሲያቋቁም ቆይቷል፡፡ በእስካሁኑ ሒደትም የአበባና አትክልት፣ የጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ዘርፍ የሚከታተሉ ተቋማት መመሥረታቸው ይታወቃል፡፡ 
በዚሁ ቅርጽ አገሪቱ የምትታወቅበትና ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስገባው ቡና ራሱን የቻለ ቦርድ እንዲቋቋምለት ሐሳቡ ቀርቦ በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ 
በአሁኑ ወቅት ቡና ከምርት ጀምሮ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስኪደርስ ድረስ በግብርና ሚኒስቴር ባለቤትነት ይካሄዳል፡፡ ከምርት ገበያ እስከ ኤክስፖርት ድረስ ያለው ሒደት በንግድ ሚኒስቴር ባለቤትነት ይከናወናል፡፡ ቡና በንግድ ሚኒስቴር ውስጥ እንደማንኛውም የግብርና ምርት የሚታይ በመሆኑና ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ፣ በግብይት ሒደት ከፍተኛ ችግሮች መፈጠራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ ዘገምተኛ መሆኑን በዘርፉ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ 
እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ የቦርዱ መቋቋም ቢዘገይም አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ በንጉሡ ዘመን የቡና ቦርድ የሚባል ተቋም ነበር፡፡ በወታደራዊው መንግሥት የሥልጣን ዘመንም የቡናና ሻይ ሚኒስቴር በመባል ነበር፡፡
ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር የቡና ዘርፍ ትኩረት እያጣ መምጣቱን የሚናገሩት የቡና ነጋዴዎች፣ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ ሲገባው እየቀጨጨ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ 
በአዲሱ ዓመት የቡና ቦርድ ማቋቋም የሚያስችለው ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅና ከዚያም ቦርዱ እንደሚቋቋም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር