ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተጀመረው የ15 ከተሞች የውኃ ፕሮጀክት ተቋረጠ

-    ፕሮጀክቱ የተቋረጠው የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ውሉን በማፍረሱ ነው

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓመታት በፊት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የጀመረው የ15 ከተሞች የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተቋረጠ፡፡
የፕሮጀክቱን ወጪ ብድር የሰጠው የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ውሉን ማፍረሱ ለፕሮጀክቱ መቋረጥ ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች ለሚገኙ 15 ከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻልና 500 ሺሕ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረውን ፕሮጀክት በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ 

ፕሮጀክቱ የሚፈጀውን ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወይም 36 ሚሊዮን ዩሮ በብድር የለገሱት የአውሮፓ ኮሚሽንና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በጋራ በመሆን ነበር፡፡ 

በዚህ ከፍተኛ ገንዘብ ፕሮጀክቱ በ15 ከተሞች ቢጀመርም በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የሰጠውን 16 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ውል ለማፍረስ መገደዱን ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ 

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ለፕሮጀክቱ መጓተት ኮንትራክተሮችን ወቅሰዋል፡፡ ኮንትራክተሮቹ በባንኩ የጨረታ ሕግ ተገምግመው ሥራው ቢሰጣቸውም ደካማ በመሆናቸው ፕሮጀክቱን በጊዜው መፈጸም አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ከኮንትራክተሮቹ ላይ ለመንጠቅ በባንኩ አሠራር የተነሳ በመቸገሩ ሥራው መጓተቱን፣ በውሉ መሠረት ፕሮጀክቱ በጊዜው ባለመጠናቀቁ ውሉ ሊቋረጥ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጉዳት በመነሳትም የውኃ ሥራ ኮንትራክተሮች ከዚህ በኋላ ፈቃዳቸውን ሊያድሱ የሚችሉት ብቃታቸው ተገምግሞ እንደሚሆን፣ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ጉዳት ያደረሱትንም ፈቃዳቸውን ባለማደስ ለመቅጣት ሚኒስቴሩ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የ15 ከተሞች የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ከቆሙበት ለማስቀጠል ከባንኩ ጋር ድርድር በመደረግ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር