የደቡብ ክልል ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ከ15 ነጥብ 4ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 07/2005 (ዋኢማ) - የደቡብ ክልል ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ዘንድሮ በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ማስፈፀሚያ ከ15 ነጥብ 4ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ ፡፡ 

ምክር ቤቱ ያፀደቀው በጀትም ከቀዳሚው ዓመት ከ1 ቢሊዮን 480 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል፡፡ 

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለብርሃን ዜና በጀቱን ለክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ አቅርበው ባጸደቁበት ጊዜ እንደተናገሩት በጀቱ ለመሰረተ ልማት ፣ ለድህነት ተኮር ፕሮግራሞች፣ ለምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችና ለመልካም አስተዳደር ስራዎች ማስፈጸሚያ ይውላል፡፡ 

ለክልሉ ከተመደበዉ በጀቱ ዉስጥ ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚበልጠው ከፌዴራል መንግስት የቀመር ጥቅል ድርሻ፣ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ከክልሉ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የሚሰበሰብ ሲሆን ከ3 ቢሊዮን 015 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ለምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ የሚገኝ ነዉ ። 

እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ገንዘብ 6 ሚሊዮን 882 ሺህ ብር በብድር ፣ 116 ሚሊዮን 842 ሺህ ብር ከእርዳታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

አጠቃላይ ከተመደበው በጀት ውስጥም ለታችኛው የአስተዳደር እርከን በዓላማ የተገደበ በጀት 76 በመቶ ሲሆን ቀሪው 24 በመቶ ለክልሉ ቢሮዎች የተያዘ መሆኑን አቶ ኃይለብርሃን ገልፀዋል፡፡ የበጀት ክፍፍል ሲደረግ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና ልማት ስራዎች፣ መስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ፣ እንዲሁም የአስተዳደርና ሌሎች ሴክተሮች ወጪ በጥልቀት እንዲካተት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዴሴ ዳልኬ በሰጡት አስተያየትም የክልሉ በጀት የተደለደለዉ ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ በሚሆኑበት አግባብ ነው ብለዋል፡፡ 

የተመደበው በጀትም ድህነት ተኮር የሆኑ ተግባራትን ፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ትኩረት የተሰጠዉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

እንደ ኢዜአ ዘገባ መላው የክልሉ ህዝብ በየደረጃው የሚበጀተውን ገንዘብ በማወቅ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን መከታተልና ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገቢ ለመሰብሰብ በሚደረገው ርብርብ የነቃ ተሳፎ በማድረግ የሚበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
http://www.waltainfo.com/index.php/2013-07-12-15-28-45/9246--7-15-4-

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር