ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በደቡብ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተመረጡት የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደሴ ዳልኬ ሥራቸውን በይፋ ጀመሩ

የሲዳማ ብሔር ተወላጅ የሆኑት አቶ ደሴ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙት ከቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ላይ የክልሉን መንግሥት ኃላፊነት ተረክበዋል፡፡

አቶ ደሴ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማዕከል የሆነውን የደቡብ ክልል ኃላፊነት ሲረከቡ እንደተናገሩት፣ ለሕዝቡ እኩል የልማት ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ የክልሉን ሕዝብ አንድነት ለማጠናከርና የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ምንም እንኳን በክልሉ ሴክተር መሥርያ ቤቶች ከዚህ ቀደም ባይሠሩም፣ ከ1996 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም የይርጋ ዓለም ከተማ ከንቲባ፣ ከ1998 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ትምህርት መምርያ ኃላፊ፣ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ሰኔ ወር ድረስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን የሠሩ ሲሆን፣ ከሐምሌ 6 ቀን ጀምሮ አዲሱን ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ በባይሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በለውጥ አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ደሴ፣ በአዲሱ ሹመት የተሻለ ለውጥ ያስመዘግባሉ ተብሎ እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በዞን ደረጃም ሆነ በፌደራል ደረጃ የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ለዚህ ኃላፊነት እንዳበቃቸው በክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ከተሳታፉ ግለሰቦች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡ “አቶ ደሴ በተለይ በሲዳማ ዞን አስተዳዳሪነታቸው ወቅት ባሳዩት አመራር የተነሳ ክልሉን በፍትሐዊነት ያስተዳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤” ሲሉ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል ሰባተኛ ጉባዔ ላይ ከተሳታፉ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል፣ የሳይንስና ቴከኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በአቶ ደሴ ላይ ትልቅ እምነት አሳድረዋል፡፡ “አዲስ ከተመረጡት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ጋር ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል ሠርተናል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሆነው ሳውቃቸው ጥሩ ዕውቀት ያላቸው፣ ሰው አክባሪና የሚሠሩት ጠንቅቀው የሚያውቁ እንደነበሩ እመሰክራለሁ፤” ብለዋል፡፡

ደቡብ ክልል አቶ ደሴን በማግኘቱ ዕድለኛ ነው የሚሉት ዶ/ር አሸብር ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብስብ በሆነው ፓርላማ በነበራቸው ግንኙነት የሥራ ባልደረባና አጋር ሆነው ነበር ያሳለፉት፡፡ ከዚህ አኳያ የሲዳማ ብሔር አባል ቢሆኑም፣ ከዚህ ቀደም አቶ ዓባይ ፀሐዬ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እንደገለጹት አቶ ደሴም ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ካፋ፣ ጋሞ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እሳቸውም በዚያ ዓይነቱ መንገድ የተቀረፁ ናቸውና፡፡ ሁሉንም ብሔረሰቦች በእከኩልነት የሚያዩና ሁሉንም እንደራሳቸው ብሔር አድርገው ማየት የሚችሉ ሰፊና ምሉዕ ሰው ናቸው፤” በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

ዶ/ር አሸብር ቀድሞ ሲል በነበሩት ርዕሰ መስተዳድር የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በአቶ ደሴ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ የራሳቸውንም ራዕይና ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህም በአጠቃላይ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅዱን እንደሚያሳኩ ጥርጥር አይኖረውም ብለው፣ “ከምርጫው እነደተረዳሁትና የጉባዔውንም መንፈስ እንዳየሁት የሁሉም ሰው እምነት ይኼ ነው፤” በማለት አስተያየታቸውን አጠናቅረዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የክልሉ ሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ኢሕአዴግ አቶ ደሴን ለዚህ ኃላፊነት በማቅረቡ ምርጫው ትክክል ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የክልሉን ሕዝብ አንድነት ለማጠናከር የተሻለ ግንዛቤና ተነሳሽነት ያላቸው ናቸው ሲሉም ገልጸዋቸዋል፡፡

አቶ ደሴ ሥራቸውን በይፋ ሲጀምሩ እንደተናገሩት፣ በተያዘው የበጀት ዓመት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝልማት ዘርፍ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ከ200 ሺሕ በላይ ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ፡፡ በክልሉ በሚገኙ 14 ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጐች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር