ሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ከ4 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን በቅድመና ድህረ ምረቃ ኘሮግራም ዛሬ አስመረቀ

አዋሳ ሐምሌ 06/2005 የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በ2006 የትምህርት ዘመን ለሚያካሄዳቸው ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከመንግስት የተመደበለት መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት ገለጹ፡፡ ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸው ከ4 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞ ዛሬ አስመርቋል፡፡ በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው በ2006 የትምህርት ዘመን በአራት ፕሮግራሞች ሰባት ውጤቶች ላይ በማተኮር 57 ዋና ዋና ተግባራትን ለማከናወንና 40 ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ ዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ የህብረተስብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማካሄድ አኳያ በ2005 የበጀት አመት ከመንግስት በተመደበለት ከ975 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ መጠነ ሰፊ ስራዎችን ማከናወኑንም አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ሰራዎች ዩኒቨርስቲው የቅበላ አቅሙን ለማሰደግና የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንዳለው አመልክተው መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈው 70 በመቶ የቴክኖሎጂና ተፈጥሮ ሳይንስ መስክና 30 በመቶ ማህበራዊ ሳይንስ ሀገራዊ የተማሪ ቁጥር ምጣኔ ሙሉ በሙሉ መተግበሩን አስታውቀዋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የትምህረት ዘርፎች ተግባራዊ ያደረጉት አዱሱን ተማሪ ተኮር የሞጁለር የትምህርት አሰጣጥ ዘዴና ተከታታይ የተማሪዎችን ውጤት ምዘና ስርዓት አጠናክሮ በመቀጠል ከዚህ ቀደም ከትምህርታቸው ይሰናበቱ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዘመኑ ለመማር ማስተማር የሚያግዙ የተለያዩ የትምህርት ግብኣቶችን የማሟላትና የማደራጀት ስራዎች መከናወናቸውን ዶክተር ዮሴፍ ጠቁመው በተጨማሪም የትምህርት አሰጣጡን በቴሌ ኮንፍረንስ እንዲታገዝ መደረጉ ለትምህርት ጥራት መጎልበት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ አቅርቦትን ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለማሻሻል የዲዛይን ስራው ተጠናቆ ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተከላና የዝርጋት ስራ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ለ14ኛ ጊዜ በወንዶ ገነት ደንና የተፈጥሩ ሀብት ኮሌጅ ከአንድ ሳምንት በፊት የተመረቁትን ፣ በሀዋሳ ግብርናና በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ነገ የሚመረቁትን ጨምሮ 4 ሺህ 723 ተማሪዎችን ለምረቃ በቅተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 556 በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ የማስተርስ ተማሪዎች መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡ ዩኒቨርስቲው ከ14 አመት በፊት ሲመሰረት በቅድመ ምረቃ የነበሩት ስምንት የስልጠና መስኮች ወደ 59 በድህረ ምረቃም 43 ፕሮግራሞችን ሲከፍት ከዚህም ውስጥ ሰባቱ የዶክትሬት ድግሪ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ የተማሪዎችም ቁጥር ከ2 ሺህ 300 ወደ 29 ሺህ 558 ለማሳደግ መቻሉንና ከእነዚህም ውስጥ 6 ሺህ 400 የሚሆኑ ሴቶች መሆናቸውም በምረቃው ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር