የ121 ዓመት አድሜ ባለጸጋ የሆኑት የአቶ ጠቀቦ ሾታ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ::

ዲላ ሐምሌ 02/2005 የጌዴኦ አርሶ-አደር በነፍጠኛው ስርዓት ላይ ባካሄደው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት እና የ121 ዓመት አድሜ ባለጸጋ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ ። የአቶ ጠቀቦ ሾታ ቀብር በጌዴኦ ባህላዊ ስነ-ዓስርዓት በዲላ ዙሪያ ወረዳ ዛሬ ተፈጸመ ። አቶ ጠቀቦ ሾታ ከአስራ ሁለት ሚስቶቻቸው ሰማንያ ሰባት ልጆች እና ከአንድ ሺህ በላይ የልጅ ልጅ ያፈሩ እንደነበሩም በቀብር ስነስረአቱ ላይ በተነበበዉ የህይወት ታሪካቸው ላይ ተገልጿል ። አቶ ጠቀቦ ሾታ በ1884 ዓመተ ምህረት በዲላ ዙሪያ ወረዳ ሚቺሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መወለዳቸዉን ቀብር ስነ-ስርዓታቸው ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል ። በጌዴኦ አርሶ አደር ላይ ይደርስ የነበረውን የጭቆና አገዛዘ በጽኑ በመቃወም በ1952 ዓመተ ምህረት በነፍጠኛው ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘር የሚቺሌን ድል ካስመዘገቡ አባቶች መካከል አንዱ ነበሩ ። አቶ ጠቀቦ ሾታ ከዚህ የትጥቅ ትግል በመለስ በጌዴኦ ብሄርና በአጎራባች ወረዳዎች እና ክልል ህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲሰፍን በማድረግና ግጭቶች እንዳይከሰቱ የበኩላቸውን ከመወጣታቸውም ባሻገር የጌዴኦ ባህልን ለማሳደግ የዞኑን ልማት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተጠቁሟል ። በህዝባዊ ውይይቶች ህብረተሰቡን በመወከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ በመሆን ለጌዴኦ ህዝብ እድገት የበኩላቸውን መወጣታቸውንና ለፈጸሙት መልካም ተግባር በጌዴኦ ባህል ለጀግና የሚሰጠውን የሀይቻነት ማእረግም ማግኘታቸውም ተመልክቷል ። የረጅም እድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ ጠቀቦ ሾታ የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ የደቡብ ብሄር ብሄርሰቦችና ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የጌዴኦ ዞን ካቢኔ አባላት የስድስቱም ወረዳና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ቁጥሩ በርካታ ህዝብ ተገኝቷል ። አቶ ጠቀቦ ሾታ ከአስራ ሁለት ሚስቶቻቸው ሰማንያ ሰባት ልጆች እና ከአንድ ሺህ በላይ የልጅ ልጆች ያፈሩ እንደነበሩም በህይወት ታሪካቸው ላይ ተገልጿል ።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=9434&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር