የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ አዋሳ በሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ከህገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ተገልጋዮችን አንገላተዋል ያላቸውን 11 ሰራተኞች በህግ ቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2005 (ኤፍ.ቢ. ሲ) የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ በስራዬ ላይ እንቅፋት ሆነዋል ባላቸው የተቋሙ ሰራተኞችና ህገወጥ ደላሎች ላይ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር በመሆን በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አደረገ፡፡
በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉት ተቋሙ አዋሳ በሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ከህገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ተገልጋዮችን አንገላተዋል ያላቸውን አስራ አንድ ሰራተኞቹ ፡፡
የኢሚግሬሽን ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ የሚሰጠው አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አይደለም በዚህም ለእንግልት እየተዳረግን ነው የሚሉና መሰል አቤቱታዎች በተገልጋዩ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎች ናቸው፡፡
ተቋሙ የችግሩ መንስኤዎች የህግ ወጥ የደላሎች መበራከትና አሁን ካለው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ተያይዞ የመጣ መሆኑን በመግለፅ  ፤ ለዚህም ያካሄድኳቸው ግምገማዎችና ክትትሎች ማሳያ ናቸው ብሏል፡
የዋና መምሪው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሀይለ ጊዮርጊስ እንደሚሉት ፥ አዲስ አበባ በሚገኘው ዋናው ተቋም የሚስተዋለው የአገልግሎት መጨናነቅ ህገወጥ ደላሎች ለፓስፖርት ፈላጊዎች በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡
“በክልሎች ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ  ስድስት መስሪያ ቤቶች ቢኖሩም ህገወጥ ደላሎቹ ተጨማሪ ብር ለማግኘት ትክክለኛው ፓስፖርት ያለው አዲስ አበባ ነው በማለትና ተገልጋዩን ቪዛ እናመጣላችዋለን እያሉ  ፓስፖርታቸውን እየቀሙ ይወስዳሉ " ብለዋል፡፡
በህገወጥ ደላሎችና በአንዳንድ የተቋሙ ሰራተኛች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የጥቅም ትስስርም ሌላኛው የችግሩ መንስኤ መሆኑን ነው አቶ ጌታቸው ያስረዱት፡፡
ህገወጥ ደላሎቹ ከሰራተኛቹ ጋር በመመሳጠር ባለጉዳዮች ገንዘብ ከከፈሉ ፓስፖርት የሚወሰድበትን ቀጠሮ እናሳጥርላቸዋለን በማለት የተቋሙ አንዳንድ ሰራተኛችም ከተገልጋዮች ጉቦ እየተቀበሉ ከደላሎች ጋር አላስፈላጊ ድርጊቶችን በመፍጠር አግልግሎቱን ሲያዛቡ የነበሩ ናቸው  ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተቋሙ የሚስተዋለውን መጨናነቅ በመፍታት ለተገልጋዩ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ተቋሙ በቂ ጥናት በማድረግ ህጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
“እነዚህ የስነምግባር ችግር የታየባቸው ሰራተኛ በአንዳንዶቹ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በሌሎቹ ላይ ደግሞ ወደህግ የመውሰድ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን ፥ በዚህም ረገድ አዋሳ ከተማ በሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት አስራ አንድ  ሰራተኞች ላይ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ በማውጣት በቁጥጥር እንዲውሉ ተደርጓል" ብለዋል፡፡
በፓስፖርት ፈላጊዎች ላይ እንግልት በመፍጠር ላይ የሚገኙ ህገወጥ ደላሎችና ሰራተኞችን በማጋለጥ ተቋሙ የጀመረውን አሰራር በመደገፍ ረገድም ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን በመጠቆም የበኩሉን እንዲወጣ መጠየቃቸውን የኢሬቴድ ዘግቧል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር