በመጪዎቹ 10 ቀናት በርካታ ቦታዎችን የሚሸፍን ዝናብ ይኖራል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2005 (ዋኢማ) - በመጪዎቹ አሥር ቀናት በመደበኛ ሁኔታ የክረምት ዝናብ ሰጪ ክስተቶች በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመጠናከራቸው ጋር ተያይዞ ብዙ ቦታዎችን የሚሸፍን ዝናብ እንደሚኖር ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ 

በመጪዎቹ ቀናት ዝናብ ሰጪ ክስተቶች በአብዛኛው የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል፡፡ 

በመሆኑም አብዛኛውን የወቅቱን ዝናብ ተጠቃሚዎች የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ እንደሚኖርና አልፎ አልፎም በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ከባድ ዝናብ ይከሰታል፡፡ በዚሁ መሠረት የትግራይና የአማራ ምዕራባዊ አጋማሽ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላ፣ የምዕራብና የመካከለኛው ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አብዛኛው ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ፡፡ 

እንዲሁም የምሥራቅ አማራና ትግራይ፣ የአፋር፣ የምሥራቅ ኦሮሚያ፣ የድሬዳዋ፣ የሐረሪና የሰሜን ሶማሌ አካባቢዎች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡ በተጨማሪም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በረዶ የቀላቀለና ነጎድጓዳማ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር የጠቀሰው የኤጀንሲው መግለጫ ቀሪዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ብሏል፡፡

በነዚሁ ቀናት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንዲሁም ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ በሚጠበቅባቸው የአገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢዎች የሚገኘው ዝናብ ለመኸር እርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር የተገኘውን እርጥበት በመጠቀም የወቅቱን እርሻ ለማካሄድ ያስችላል፡፡ 

በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ የሚጠበቀው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በተዳፋትና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እርሻ ማሳዎች ላይ የአፈር መሸርሸርና የውሃ መተኛት ሊያጋጥም ስለሚችል አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኤጀንሲው አሳስቧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር