የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ በመፋጠን ላይ ይገኛል

የስታዲየሙ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 23 በመቶ ያህል የተጠናቀቀ ሲሆን ከተያዘለት የጊዜ ገደብ አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፤

በቀድሞ አጠራሩ «ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስታዲየም» በአሁኑ ደግሞ «አዲስ አበባ ስቴዲየም » የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ የአገሪቱንና የክለቦችን ዓለም አቀፍ ውድድሮች የምታስተናግድበት ብቸኛው ስፍራ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ሠላሳ አምስት ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው የሚነገርለት የአዲስ አበባ ስቴዲየም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1940 እንደተገነባ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ስታዲየሙ በአውሮፓውያኑ 1962፣ 1968ና 1976 የተካሄዱ ሦስት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል። ኢትዮጵያ ካስተናገደቻቸው ከእነዚህ ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች መካከል ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ባለድልም ሆናበታለች።
አዲስ አበባ ስታዲየም የአፍሪካ የወጣቶች ሻምፒዮናና 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም በብቃት ተስተናግደውበታል።
ይህ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውና በመዲናዋ በብቸኝነት ደከመኝ ሰለችኝ ሳይል ከአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች በተጨማሪ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚካሄዱበት ስታዲየም «አንድ ለእናቱ » እየተባለ የሚጠራበት ጊዜ ማብቂያ የተቃረበ ይመስላል።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በባሕር ዳር፣ በመቀሌ፣ በነቀምትና በሐዋሳ ከተሞች በመገንባት ላይ የሚገኙት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ። ከእነዚህ ስታዲየሞች መካከል ግንባታው ከተጀመረ የአንድ ዓመት እድሜ ያስቆጠረው የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ በመፋጠን ላይ ይገኛል። የጋዜጣው ሪፖርተር በከተማዋ በነበረው ቆይታም ይህንን አስተውሏል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለግንባታው በመደበው 548 ሚሊዮን ብር በሳትኮን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ ተቋራጭነትና በኤምኤች ኢንጂነሪንግ አማካሪነት በመሠራት ላይ የሚገኘው የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ 23 ነጥብ አምስት በመቶ ተጠናቅቋል።
ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 40ሺ ተመልካቾችን በመቀመጫ እንደሚይዝ የሚጠበቅ ሲሆን ፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የኦሊምፒክ ደረጃ ያለው እንደሆነ የፕሮጄክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ጉተማ ለጋዜጣው ሪፖርተር ነግረውታል። ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት የሐዋሳ ስታዲየም እግር ኳስን ጨምሮ የአስራ አንድ ስፖርቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ይዟል።
ግንባታው ያለበትን ደረጃ ሲገልጹም በአሁኑ ሰዓት የተመልካቾች መቀመጫ ሥራ መጠናቀቁንና ሌሎች ስራዎችም በፍጥነትና በጥራት እንዲሁም በወጣለት የጊዜ ገደብ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት ።
የሐዋሳ ስታዲየም ፕሮጄክት በስኬት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥትና ስፖርት ኮሚሽን በየቀኑ በግንባታው ስፍራ እየተገኙ የሞራል ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በወቅቱ በማቅረብ ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አቶ ያሬድ ገልጸዋል።
በሥራ ሂደቱ እስካሁን የጎላ ችግር እንዳላጋጠመ የሚገልጹት አቶ ያሬድ፤ የክልሉን መንግሥት፣ የክልሉን ስፖርት ኮሚሽን፣ የሥራ ተቋራጩንና የአማካሪውን ተባብሮና ተግባብቶ መስራት የስታዲየሙ ግንባታ ከታለመለት ጊዜ በፊት ሊጠናቀቅ እንደሚችል አመላካቾች እንደሆኑም አስረድተዋል።
የሐዋሳ ስታዲየም ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ አብነት ኃይሌ ድርጅታቸው ከስታዲየሙ ዲዛይን ጀምሮ በማማከር ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው፤ ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜና የጥራት ደረጃ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ድርጅታቸው በባሕርዳር፣ በነቀምትና በሐዋሳ ስታዲየሞች ግንባታ ላይ በአማካሪነት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የሐዋሳው ስታዲየም ከቀድሞዎቹ በርካታ ልምዶች የተቀሰሙበትና በርካታ አዳዲስ ነገሮች የተጨመሩበት መሆኑን ነው የሚናገሩት። ለአብነትም የሐዋሳው ስታዲየም የክብር እንግዶች መግቢያና መቀመጫ የተለየ እንዲሆን መደረጉን ይገልጻሉ።
የግንባታውን ጥራት በተመለከተም ለግንባታው የሚውሉትን ግብአቶች በቤተ ሙከራ ከመቆጣጠር አንስቶ የሚጠበቅበትን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ነው የሚገልፁት። ፕሮጄክቱ አሁን ባለው ፍጥነት የሚሄድ ከሆነ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በፊት ሊጠናቀቅ እንደሚችል በመግለጽም የአቶ ያሬድን ሃሳብ ይጋራሉ።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ መዘረዲን ሁሴን በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በግንባታው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩ ችግሮቹን የሚፈቱና አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጡ የቴክኒክና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራውን በመምራት ላይ ይገኛል ባይ ናቸው።
ኮሚቴዎቹ ለግንባታው የሚውል የፋይናንስ እጥረትና የግብአት ችግሮች ሲከሰቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት ግንባታው በታቀደለት ጊዜ ወይም ከዚያ ቀድሞ እንዲጠናቀቅ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት ለግንባታው መጠናቀቅ ለሥራ ተቋራጩም ሆነ ለአማካሪው ድርጅት የቅርብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈም በየጊዜው ክትትል እንደሚያደርግ አቶ መዘረዲን ተናግረዋል። ከግንባታ ግብአቶች ዋጋ ንረትና ተያያዥ ችግሮች ጋር በተያያዘ የስታዲየሙ ግንባታ ፈጽሞ እንደማይስተጓጎልም አረጋግጠዋል።
የስታዲየሙን ግንባታ ሲጎበኙ ካገኘናቸው መካከል ዶክተር ይልማ በርታ «ግንባታውን ሲመለከቱ ከፍተኛ የመደመም ስሜት ተሰምቶኛል » ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት የሐዋሳውን ስታዲየም ጨምሮ በክልሎች በመገንባት ላይ የሚገኙት ስታዲየሞች የአገሪቱ የስፖርት ዘርፍ እያደገ ነው የሚለው አባባል ማሳያ ናቸው ።
በመገንባት ላይ የሚገኙት አራት ታላቅ ስታዲየሞች ግንባታ በፍጥነት መካሄዳቸውና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መገንባታቸው ልዩ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ስቴዲየሞቹ ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ታላቅ ውድድሮችን እንድታዘጋጅ እድል እንደሚፈጥርላትም አብራርተዋል።
በክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስቴዲየሞች መገንባታቸው ብቁና ጥራት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማፍራት ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በመሳተፍ ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት መካከል አብዛኛዎቹ ሐዋሳ ከተማ የሚገኘው የኮረም ሜዳ ያፈራቸው ናቸው። ስታዲየሙ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከአሁን በተሻለ መልኩ በርካታ ተጫዋቾችን ለማፍራት እንደሚያስችለው ይጠበቃል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር