ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ

አዋሳ ግንቦት 30/2005 የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ከሁሉም የትምህርትና የምርምር ዘርፎቹ ጋር አቀናጅቶ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሰቲው ተማሪዎችና መምህራን አለም አቀፍ የአካባቢ ቀን በችግኝ ተከላ፣ በጽዳት ዘመቻ፣ በእግር ጉዞና በፓናል ውይይት ትናንት በሀዋሳ ከተማ አክብረዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ዩኒቨርስቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዶክተር ንጋቱ ረጋሳ እንደገለጹት ተፈጥሮን በመንከባከብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በዕወቀት ላይ የተመሰረተና ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃና ልማት ወሳኝ ነው፡፡ ዪኒቨርስቲው በዚህ ረገድ በተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ የምርምር ፕሮግራሞች በግብርናው ዘርፍ እንዳሉት ጠቁመው ይህንን ከሁሉም የትምህርትና የምርምር መስኮች ጋር አቀናጅቶና አስፋፍቶ ለመስራት ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ዲፓርትመንት ስርዓተ ትምርህርት ሲቀርጽ የአካባቢን ጥበቃ ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት መስራት እንዳለበት ፕሮፌሰር ንጋቱ ገልጸው በተማሪዎችና በመምህራን የተቋቋመው የአካባቢ ጥበቃ ክለብ ተጠናክሮ ሁሉንም ማህበረሰብ በማሳተፍ እንዲቀሳቀስ ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በአካባቢ ላይ የሚሰሩ ምርምሮችን ዩኒቨርስቲው ያበረታታል ያሉት ፕሮፌሰሩ የአካባቢው ህብረተስብ ስለጉዳዩ ያለውን ግንዛቤ ለማጎልበት በማህበረሰብ ሬዲዮ ጭምር በመጠቀም እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ እንዲሁም ከክልሉ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ግንኙነታቸውን አጠናክረው ህዝቡም ከትምህርትና ምርምር ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እሰሩ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ ዘንድሮ በሀገሪቱ ለ20ኛ በአለም ለ40ኛ ጊዜ የተከበረው የአካባቢ ቀን "አሰብ ፣ተጠቀምና አድን" በሚል መሪ ቃል እንደሆነ አመልክተው ይህም የአካባቢ ጥበቃን ከሰው ልጅ ህይወት፣ የምግብ ፍጆታና ፍላጎት፣ ከደን ልማት ጋር የተቆራኘ ሰፊ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የአካባቢ ጥበቃ ክለብ አባልና መምህራን የሆኑት ወይዘሪት እንግዳሰው ፈለቀና አቶ ምህረተአብ አብረሃም በበኩላቸው ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥተው ከመማር ማስተማሩ ጎን የአካባቢው ህብረተሰብ የሀዋሳ ሀይቅን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ከብክለትና ከጥፋት ለመታደግ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃን ከክልሉ ብሎም ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያገናዘቡ ምርምሮችና ጥናቶች በማድረግ ለፖሊሲ አውጪዎች አቅጣጫ የሚሆኑ ውጤቶች እያዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የተቋቋመው ክለብም ከዩኒቨርሰቲው ማህበረሰብ ውጪ ሌሎችን በአባልነት በማሳተፍ ጭምር የተፈጥሮና የአካባቢን ሀብት ለመጠበቅና ለመንከባከብ በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የጂኦግራፊና የአካካባቢ ጥናት የ3ኛ አመት ተመራቂ ተማሪ ደረሰ ዳንፍሌ በሰጠው አስተያየት ከብክለትና ከጥፋት የጸዳ አካባቢን የመፍጠርና የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠበቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በማመን በበዓሉ በመሳተፍ ከጓደኞቹ ጋር ያደረገውን በጉ አድራጎት ወደፊት አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የዘንድሮን የአካባቢ ቀን በዩኒቨርስቲው ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያክበሩ በርካታ ተማሪዎችና መምህራን የተሳተፉበት ከ1ሺህ በላይ የዛፍ ችግኞች በከተማው የተለያዩ ቀበሌዎችና በዪኒቨርሰቲው ቅጥር ግቢ ተክለዋል፡፡ እስከ ሀዋሳ ሀይቅ በእግር በመጓዝ ህብረሰቡን በመቀስቀስና በማስተማር የጽዳት ዘመቻ ከማካሄዳቸውም በላይ ዕለቱን አመልክቶ የተለያዩ ጥናታዊ ዕሁፎች የቀረቡበት የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=8460&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር