አስገዳጁ የቁጥጥር ደረጃ ጊዜ ገደብ የግል ጤና ተቋማትን ሥጋት ውስጥ ከትቷል

ሁኔታውን የሚያጤን ቡድን እየተዋቀረ ነው
በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ተዘጋጅቶ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የፀደቀው አስገዳጅ የጤና ተቋማት የቁጥጥር ደረጃ ጊዜ ገደብ እንዳሠጋቸው የግል ክሊኒኮች አስታወቁ፡፡
 ለአዳዲስ የጤና ተቋማት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለነባሮች ደግሞ ከፀደቀ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸው የቁጥጥር ደረጃ፣ 39 ዓይነት የጤና ተቋማትን መስፈርት ያስቀምጣል፡፡ 
በመድኃኒት ቁጥጥርና አስተዳደር ባለሥልጣን የቁጥጥር ደረጃ ዝግጅትና አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር የሺዓለም በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደረጃው የመንግሥት እንዲሁም የግል ተቋማትንም የሚመለከት ሲሆን ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የጤና ጣቢያዎችንና ጤና ኬላዎችን ጭምር ያካትታል፡፡ 
እሳቸው እንደሚሉት፣ ከፍተኛ ክሊኒክ የሚባሉት ልዩ የሕክምና ማዕከላት (Specialty Center) መሆን የሚችሉ ሲሆን፣ ለዚህ በትንሹ አሥር አልጋዎች፣ ሁለት ስፔሻሊስት ሐኪሞች እንዲሁም ፋርማሲ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህን ማሟላት ካልቻሉ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት የተመላላሽ ታካሚ አልጋ ኖሯቸው በአንድ ስፔሻሊስት ሐኪም አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጥ መካከለኛ ጤና ተቋም መሆን ይችላሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ማሟላት እንደሚችሉ የመስፈርት አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ 
ክሊኒኮች የባለሙያ እጥረትን እንዲሁም የቦታ ጥበትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ቅሬታዎችን ያሰሙ ሲሆን፣ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የከፍተኛ ክሊኒክ ባለቤት “ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የቻልነውን ያህል መስፈርቶቹን አሟልተን ለመቀጠል እንሞክራለን ካልሆነ ግን እንዘጋለን፤” በማለት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሌሎች የተወሰኑ የግል ክሊኒኮችም ቅሬታቸውን እንዲሁ ገልጸዋል፡፡ የወቅቱን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታና አቅም የማያገናዝብ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ 
ከቁጥጥር ደረጃው መፅደቅ በፊት በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና በአገልግሎት ሰጪዎች (ጤና ተቋማት) መካከል የጋራ ውይይት መደረጉንና ተመሳሳይ ቅሬታዎች ተነስተው እንደነበር ያስታወሱት የመድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀው፣ “ኅብረተሰቡ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት አለበት፡፡ ሙሉ በሙሉ በነርስ መሥራት አይቻልም፡፡ የቦታ ችግር ካለም ባላቸው ቦታ የሚፈቀደውን አገልግሎት ብቻ ነው መስጠት ያለባቸው፡፡ የቁጥጥር ደረጃው ተግባራዊ ሳይሆን ጊዜ በገፋ ቁጥር ኅብረተሰቡ ይጎዳል፡፡ በተሻለ ውድድር የተሻለ አገልግሎት ሊሰጥበት ሲችል ሴክተሩንም ማቀጨጭ ነው፤” ብለዋል፡፡ 
እሳቸው እንደሚሉት የቁጥጥር ደረጃውን በሚመለከት ባለሙያዎች ከመፅደቁ በፊት የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ በማስገባት ተወያይተዋል፡፡ በሒደትም እየታዩ የሚስተካከሉና የሚሻሻሉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመንግሥት የጤና ተቋማት ከቁጥጥር ደረጃው አንፃር ያሉ ክፍተቶችን መፈተሽ የጀመሩ ክልሎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ 
“የግል የጤና ተቋማት መጀመሪያም ቢሆን የጊዜ ገደቡ ያንሳል በማለት ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ የቁጥጥር ደረጃው ከፀደቀ አንድ ዓመት ሆኗል፡፡ ይህ ማለት ለነባር የጤና ተቋማት ደረጃው ተግባራዊ ለመሆን የቀሩት ስድስት ወራት ናቸው፤” ዳይሬክተሩ ብለው፣ የአገልግሎት ሰጪዎችን፣ የተገልጋዮችንና የሚመለከታቸውን ሌሎች አካላት አስተያየት የሚሰበሰብና ችግሮችን የሚቃኝ ከቁጥጥር ባለሥልጣኑና ከደረጃዎች ኤጀንሲ የተውጣጣ አንድ ቡድን እየተዋቀረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር