የዘመን መለወጫ በሲዳማ

በሲዳማ የጊዜ አቆጣጠር መሰረት የሳምንቱ ቀናት በስም አራትናቸው። እነሱም ቃዋዶ፣ ቃዋላንካ፣ ዴላ፣ዲኮ በሚል መጠሪያ ተለይተው የታወቃሉ። እንዲሁም አንድ ወር አጋና (ጨረቃ) እና ቱንሲቾ(ጨለማ) ተብሎ በሁለት ይከፈላል። እያንዳንዱ ወር በቋንቋው ተለይቶ የሚታወቅበት የራሱ መጠሪያ (ሥያሜ) ያለው ሲሆን ፤ ወራቱ አስራ ሁለት ናቸው። በነባሩ የሲዳማ ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠር ውስጥ ጷግሜ ፎቃ የሚል ስያሜ ተሰጥቶቷል።
    በነባሩ የሲዳማ የጊዜ ቀመር አቆጣጠር መሰረት በዓመት ውስጥ ያሉት አስራ ሁለት ወራት በአራት ወቅቶች የተከፈሉ ናቸው። ከዚሁ አንጻር ወቅቶቹ አሮ(በጋ)፣ሀዋዶ(ክረምት)፣በዴሳ (በልግ) እና ቢራ (መኸር) የሚል መጠሪያ አላቸው። በባህሉና በጊዜ ቀመሩ መሰረት ሲዳማ የራሱ ዘመን መለወጫ ቀን አለው።ይህም ፍቼ በሚል መጠሪያ ይታወቃል።
     የዘመን መለወጫ( ፍቼ) በአል አከባበር
    ፍቼ በሲዳማ ባህል በዓመት አንዴ በድምቀት የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል ነው። በባህሉ መሰረት አከባበሩ እስከ ሁለት ሳምንት ይዘልቃል። የፍቼ በዓል ቅደም ተከተላዊ የአከባበር ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ለአከባበሩ መነሻና መድረሻ የሚሆኑ ክንውኖች አሉ። ከእነዚህ ክንውኖች የመጀመሪያው ላኦ(ምልከታ) ነው። ላኦ ፍቼ መቼ እንደሚውል አያንቶዎች (የስነክዋክብት ተመልካቾች አረጋውያን) የጨረቃንና የከዋክብትን አካሄድ ጥምረት ተመልክተው የሚለዩት ሲሆን፤ አያንቶዎች ፍቼ ቀኑ መቼ እንደሚውል በከዋክብት ምልከታ ከለዩ በኋላ ለጎሳ መሪዎች ይገልጻሉ። የጎሳ መሪዎች ቀኑ ተገልጾ ለህብረተሰቡ እንዲለፈፍ ሲያዙ በገበያ ስፍራዎች በላላዋ (በልፈፋ) ይገለጻል። ላላዋ (ልፈፋ) የጎሳ መሪዎች ስር ባሉ ስፍራዎች የሚከወን ሲሆን ፤ ለፋፊዎች በገያ ቀን የበግ ቆዳ ረዠም ዘንግ ላይ ሰቅለው በመያዝ ገበያ ውስጥ ለህብረተሰቡ ቀኑ (ፍቼ) መቼ እንደሚውል ያበስራሉ።
    ከልፈፋ ቀጥሎ ያለው ክዋኔ ሳፎተ ቄጤላ (የቡራኬ ባህላዊ ጭፈራ) ነው። በባህሉ መሰረት ጭሜሳዎች (ብቁ ብጹዕ አረጋውያን) ፍቼ ሲቃረብ ለአስራ አምስት ቀናት በመጾም፤ ፍቼ (ዕለተ ቀኑ )ዘጠኝ ቀን ሲቀረው ሳፎቴ ቄጣላ (የቡራኬ ቄጣላሥበመጨፈር በዕለቱ ጾም ይፈታሉ። ቀጣዩ ክዋኔ አዲቻ ቄጣላ  (እውነተኛ ቄጣላ) የሚባለው ሲሆን ከአረጋውያኑ የቡራኬ ቄጣላ ቀጥሎ ባሉት የገበያ ቀናት ጎልማሶችና ወጣቶች በገበያው ለፍቼ አራት ቀን እስከሚቀር ድረስ አዲቻ ቄጣላ (እውነተኛ ቄጣላ) የሚባለውን ጭፈራ ይያያዙታል።
    በዋነኛው በፍቼ እለተ ቀን የሚከናወነው የአከባበር ሂደት የሚጀምረው ፀሀይ ከመሃል አናት ዘንበል ካለች በኋላ (ከቀኑ ዘጠኝ እስከ አስራ አንድ ሰዓት) ባለው ጊዜ የሚከናወን የሁሉቃ ስርአርት ነው። ለዚህም እያንዳንዱ አባወራ ከቤቱ ፊት ለፊት በሚገኝ ገላጣ መስክ ላይ ረዥም እርጥብ እነጨት ጫፉን መሬት ላይ በመውጋት ሁሉቃ (ቅስት) ሰርቶ በቅድሚያ እራሱ አባውራው በቅስቱ ውስጥ በመሹለክ ቤተሰቡንና ከብቱን በተራ ያሾልካል። ይህ ስርዓት  በባህሉ መሰረት ከዘመን ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ነው። ሁሉም በየቤቱ አስቀድሞ ለበአሉ ዝግጅት ስለሚያደርግ በፍቼ እለት ቀን ከአመሻሽ ጀምሮ ከአንዱ ቤት በመሄድ በአሉ ለሊቱን  በጋራ በመብላት ይከበራል። እለቱም ፈጣሪ በመባል ይታወቃል።
    በየቤቱ በዕለቱ የሚቀርበው ዓይነተኛ ምግብ ቡርሳሜ(በቅቤ የራሰ ቆጮ) እና ወተት ነው። የቡርሳሜ  (በቅቤ የራሰ ቆጮ) ማቅረቢያ ገበታ ቁመቱ አንድ ከንድ ስፋቱ ግማሽ ሜትር የሚሆን ከሸክላ የተሰራ ካብ ውስጥ ጎድጓዳ ሻፌታ  ነው። ከቤት ቤት በመሄድ በጋራ መብላቱ የሚጀምረው በቅድሚያ በአካባቢው በተለያዩ ማህበራዊ ደረጃዎች በባህሉ ትለቅ ወደሚባለው አረጋዊ ቤት በመሂድ ነው። ይህም ሳፎ(መጀመር) ይባላል።
    የአመጋገብ ሥርአቱ የሚጀምረው በእድሜ ወይንም በማህበራዊ ደረጃ ታላቅ የሆነ ሰው በሻፌታ ከተሞላ ቡርሳሜ(ምግብ) ቆንጥሮ በመበተን ፍቼ ዲርዲሮ እሊሺ (ፍቼ ከዘመን ዘመን  አድርሺን) በማለት ከባረከ  በኋላ ነው። በእንዲህ ከአንዱ ቤት ወደሌላው በመሄድ ሌሊቱን ሙሉ  የታረደ ሲበላ፤ የተረፈ ስጋ እቤት ውስጥ ካለ ስጋው ውጪ እንዲያድር ይደረጋል።ይህ የሚሆነው አዲስ ዓመት ለከብቶችም መልካም ዘመን እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው።
    ለፍቼ በአል ህብረተሰቡ ትልቅ ክበር ስላለው ቀደም ሲል በልዩ ልዩ ምክንያት የተጣለም  ካለ ፍቼ ሲቃረብ እርቅ ይካሄዳል። በባህሉ ተኳርፎ ወደ አዲሱ ዘመን መሸጋገር ነውር ነው። እንዲሁም በፍቼ ዕለተ ቀን ከቤት ውጪ ሌላጋ ማደር በባህሉ ስለማይደገፍ ለጉዳይ ወደተለያየ አካባቢ እርቆ የሄደ ሁሉ ለፍቼ ወደመኖሪያው ይሰበሰባል። የፍቼ ማግስት(ሁለተኛው ቀን) ጫምባላላ ይባላል። ጫምባላላ በቋንቋው እንኳን አደረረሳችሁ እንደማለት ሲሆን ፤ በባህሉ መሰረት በጫምባላላ እለት መሬት የማረስና እንጨት የመስበር ተግባር  አይከናወንም። በእለቱ ልጆች በእረኝነት ተግባርም ሆነ በሌላ በማንኛውም ሥራ አይሰማሩም። በጫምባላላ እለት ልጆች ተሰባስበው ከአንዱ ቤት ወደሌላው ቤት በጋራ በመሄድ ኤይዴ ጫምባላላ(እንኳን አደረሳችሁ) በማለት በየቤቱ ቡርሳሜ (በቅቤ የራሰ ቆጮ) እና ወተት እየተመገቡ እማውራዎች አናታቸው ላይ ቅቤ ይቀቧቸዋል። በእለቱ አባውራው ከብቶቹን ለእዚህ እለት ባዘጋጀው የለመለመ መሥክ አሰማርቶ ቦሌ(ከሀይቅ ዳርቻ የሚወጣ ጨዋማ አፈር ) የለመለመ መስክ ላይ በመነስነስ ከብቶቹን  አጥግቦ እያበላ ያውላል።
    በባህላዊ የጊዜ አቆጣጠሩ መሰረት ፍቼ( ዋነኛው ዘመን መለወጫ እለተ ቀን) ከሳምንቱ ቀናት በዕለተ ቀዋዶ የሚውል ሲሆን፤ ጫምባላላ (የፍቼ ማግስት) ሁሌም የሚውለው ከሳምንቱ ቀናት በዕለተ ቃዋላንካ ነው።
   ከጫምባላላ ቀጥሎ ያለው የአከባበር ሂደት በጥቅሉ ሻሺጋ የሚባል ሲሆን፤ ሻሺጋ  በአሉን በጋራ በገበያ  እንዲሁም በጉዱማሌ (በባህላዊ አደባባይ) በድምቀት የማክበር ሂደት ነው። በአከባበሩ ከታዳጊ ወጣቶች ጀምሮ እስከ አረጋውያን ያለው ህብተረሰብ በቄጣላ(በጋራ ባህላዊ ጭፈራ) ልጃገረዶች ሀገሬ (ባሀላዊ ዘፈን) ያላገቡ  ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች በፋሮ (ባህላዊ ጭፈራ) የሚሳተፉበት ከመሆኑም በተጨማሪ  የፈረስ ግልቢያ የንጉስ ስረአት የሚታይበት ነው።
   ከላይ በጥቅሉ ከተገለጠው በተጨማሪ ሻሺጋ በውስጡ ፋቂቂቾና ፍቺፋሎ የተሰኙ አበይት የአከባበር ክንውኖችን  ያካትታል። ከዚሁ አንጻር ሻሺጋ በገበያ በድምቀት የሚከበርበት ሂደት እስከሚገባደድበት ዕለት ቆይቶ በሻሺጋ መገባደጃ ዕለት ባለው የገበያ ቀን ወጣት ወንድ ለሚወዳት ሴት ልጃገረድ ፍቂቂቾ በልጅ ይልክላታል።የመፋቂያው ተምሳሌት ወይም ትርጉም ወድጄሻለው ወዳጅ ሁኚኝ የሚል ነው። መፋቂያው የተላከላት ሴት ከማን እንደተላከላት ጠይቃ ላኪውን ካልፈቀደችው መፋቂያውን አትቀበልም። የተላከውን ልጅ መልስለት ትለዋለች። ተስፋ ሳይቆርጥ በመልክተኛው ልጅ በኩል የመማጠኛና ማማለያ  ቃላት መላልሶ ይልክላታል። ልቧ ከፈቀደ ትቀበለዋለች። አልያም የወዳጅነት ጥያቄውን ካልተቀበለች መፋቂያው ለላኪው ተመላሽ ይሆናል።
    የመፋቂያው ልውውጥ ጥያቄ አንዳንዴ መፋቂያሽን ላኪልኝ የሚል ሊሆን ይችላል። ፍቄበታለሁ ላንተ አይሆንም ልትለው ትችላለች ። ይሄኛው አባባል መፋቂያ የለኝም ከማለት የተሻለ ስለሆነ የፋቅሺበተን ያንቺ ጥርስ የነካውን ፈልጌ ነው ይላታል። ወስደህ ልትጥለው ነው ከልብህ አይደለም ካለችው እንደነፍሴ እይዘዋለሁ እያለ መልሶ ይልክባታል። አባባሉና ማንነቱ  ካማለላት መቼ ትመልስልኛለህ በማለት በአንዴ የእሽታ መልስ ላለመስጠት ትግደረደራለች። ቀኑን ነግሮ ሲልክባት የትጋ የሚል ጥያቄ ልታስከትል ትችላለች። ይሄኛው ጥያቄዋ የት እንገናኝ የማለት አይነት ነው። በእንዲህ ምልልሱ ከሰመረና መፋቂያውን እንዳትጥለው እንደነፍስህ  ያዘው ብላ ከላከችለት  የወዳጅነት ጥያቄው እሽታ አገኘ ማለት ነው።
    ቀጣዩ የአከባበር ሥርአት ፍቺፋሎ(ለፍቼ በአል በጋራ ወደአደባባይ  መውጣት) የሚል መጠሪያ ያለው ነው። የፍቺላሎ እለት የአካባቢው ህብረተሰብ በጎሳ በጎሳው ሆኖ  በቄጣላ (ባህላዊ ጭፈራ ) ወደጎዱማሌ  የፍቼ በአል በጋራ ወደሚከበርበት ባህላዊ አደባባይ በመውጣት ፤ በጉዱሌ ውስጥ ባለ ማዕከላዊ ስፍራ በጎሳ በጎሳው በየተራ ገብቶ በመቀመጥ በጎሳው አረጋውያን፣ በጎሳው መሪ እና በጎሳው የባህላዊ እምነት መሪዎች ተመርቆ ተመክሮ በተመሳሳይ ቄጣላ ( ባህላዊ ጭፈራ ) በአሉን የማክበር ስርአቱን ይያያዘዋል።
ፍቺ ፋሎ ቀደም ሲል ከላይ ከተጠቀሱ የበአሉ አከባበር ሂደቶች ሁሉ የላቀ ብዙ ጎሳዎች ጉዱማሌ በመውጣት በጋራ የሚያከብሩት ደማቅ የአከባበር ስርአት የሚታይበት የፍቼ በአል ማሳረጊያ ነው። ከዚሁ አንጻር በእለቱ ቄጣላ ( የጋራ ባህላዊ ጭፈራ) የፈረስ ጉግስ ግልቢያ ትርኢት፣ ሆሬ (የልጃገረዶች ባህላዊ ዘፈን) እና ፋሮ  (ልጃገረዶችና ያላገቡ ወጣት ወንዶች በጋራ የሚሳተፉበት ባህላዊ ጭፈራ ) የሚከወንበት ደማቅ የማሳረጊያ በአል  ነው። በዚህ እለት በርካታ ሙሽሮች አምረውና ደምቀው በባሎቻቸው እናቶችና በጎረቤት ሴቶች ታጅበው ወደጉዱማሌ ይወጣሉ። በባህሉ መሰረት አንዲት ሙሽራ የሙሽርነት ጊዜዋ የሚያበቃው ተሞሽራ ከቆየችበት በእንዲህ አምራና ደምቃ ወደ ጉዱማሌ በመውጣት ነው።

http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/society/2804-2013-06-24-07-43-51

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር