የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በይፋ ተቋቋመ፤ ችግር ፈቺ የምርምርና የጥናት ስራዎችን እንዲያከናውን መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ ይሰጣል

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2005 ዛሬ በይፋ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የአገሪቱን ልማት የሚያግዝ ስኬታማ ምርምርና ጥናቶችን እንዲያደርግ ለማስቻል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው የአካዳሚው ይፋዊ የማቋቋሚያ ጉባዔ ላይ የተገኙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደሴ ዳልኬ እንዳስታወቁትአካዳሚው በአገሪቱ ችግር ፈቺ የምርምርና የጥናት ስራዎችንና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደምሴ ኃብቴ በበኩላቸው አካዳሚው ለአገሪቱ ልማት ጠቀሜታ ያላቸውን የተለያዩ የምርምር ስራዎች ለመስራት የአካዳሚው አባላት በአምስት የተለያዩ መስኮች ተከፍለው የጥናትና ምርምር ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። አካዳሚው እስካሁን በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ የምርምር ተቋማትን ግንኙነት፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጥራት፣ በግብርና እና በጤና መካከል ያለው የፖሊሲ ቅንጅት ምን እንደሚመስል ጥናት አድርጓል። አካዳሚው የሚያወጣቸው የምርምርና የጥናት ስራዎች የኅብረተሰቡን ኑሮ የመለወጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ስራዎቹ ወደ ተግባር የሚሸጋገሩበትን አሰራር እንደሚከተልም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። ፕሮፌሰር ደምሴ እንዳሉት አካዳሚው በመጪው ኅዳር ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ የሳይንስ አካዳሚ ጉባዔን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ ይገኛል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የአካዳሚው መስራች አባላት ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች በሳይንስ ማህበረሰቡ በተመረጡና ፈቃደኛ በሆኑ 49 መስራች አባላት የተመሰረተው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው። በርካታ ምሁራን እንደሚያምኑበት በዓለም ቀዳሚው የሳይንስ አካዳሚ በኔፕልስ እኤአ በ1560 ዓ.ም የተመሠረተው ሲሆን የወቅቱ መሥራቾች ፍላጎት በአስማትና በሳይንስ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሁም ሃይማኖቶች ዓለምን የሚያዩበትንና ተጨባጩ ዓለም ያለበትን ሁኔታ በሚስጥር ለመፈተሽ ነበር።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር