የአካባቢ ምርጫ ትኩረት ነፋጊዎች


በኢትዮጵያ አምስት ዓይነት ምርጫዎች ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህም ጠቅላላ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ ማሟያ ምርጫ፣ ድጋሚ ምርጫና ሕዝብ ውሳኔ ይሰኛሉ፡፡
በያዝነው ወር ሚያዝያ 6 እና 13 ቀን 2005 ዓ.ም. የተካሄደው የአካባቢ ምርጫ ውጤት በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ እንደሚሆን የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከተወዳዳሪዎች አለመመጣጠን የተነሳ ብቻውን ተወዳድሯል የሚባለው ኢሕአዴግ ምርጫው ሳይደረግ ውጤቱን ያውቀዋል፡፡ የአካባቢ ምርጫ በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ዕለትና በድኅረ ምርጫው ትኩረት እንዲነፈግ ያደረጉት ዓበይት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የአካባቢ ምርጫ በየደረጃው በሚገኙ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡ በመላው አገሪቱ የተካሄደው ምርጫ ከኢሕአዴግ ውጪ የብዙ ዜጎችን ትኩረት እንዳላገኘ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የዘገቡ ሲሆን፣ ከዚህ በተቃራኒ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ምርጫውን ‹‹ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምሳሌ የሚሆን›› ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ለዚህ ድምዳሜ ፕሮፌሰሩን ያደረሳቸው ምክንያት ደግሞ ምርጫው ሰላማዊና የተሳካ መሆኑ፣ እንዲሁም የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ከሁሉም አቅጣጫ የተረጋገጠበት መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና የጥናት ውጤቶች ግን ከምርጫ ቦርድ ይፋዊ አቋም በተቃራኒ የአካባቢ ምርጫዎች ካላቸው መጠነ ሰፊ ጠቀሜታ አኳያ የተሻለ ትኩረት እንዲያገኙ አገሪቱ ቅድሚያ ሰጥታ ልትሠራበት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የዕጩዎች ብዛት፣ የግንዛቤ ችግር፣ የፌዴራል መንግሥት ጫና፣ የፖለቲካ ባህልና የፖለቲካ ፓርቲዎች ደካማ ይዞታን በአንኳር ምክንያትነት የሚያነሱት አስተያየት ሰጪዎች እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከሕግ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከማኅበራዊ አኗኗርና ከባህል ጋር የተገናኙ የመፍትሔ ሐሳቦችን ይሰጣሉ፡፡ 

የዕጩዎች ብዛትና የፓርቲዎች ተወዳዳሪነት
በዘንድሮው የአካባቢ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 31.6 ሚሊዮን መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ 45,000 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ለመመረጥ ዕጩ የነበሩት ቁጥር ደግሞ 3.8 ሚሊዮን መሆኑን ቦርዱ ያመለክታል፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ ቁጥር ውስጥ 3.7 ሚሊዮን ዕጩ ያቀረበ ሲሆን የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን ዕጩዎች ቁጥር ካየን ልዩነቱ በውቅያኖስና በጠብታ መካከል መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 183፣ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ 85፣ ቅንጅትና ኢራፓ 42፣ እንዲሁም ኢዴፓ አንድ ዕጩ በማቅረብ ከተወዳዳሪነት ይልቅ የኢሕአዴግ አጃቢዎች መሆንን መርጠዋል፡፡ ሌሎች 33 የሚጠጉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ እንደተለመደው በመጫወቻ ሜዳውና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ እምነት የለንም በማለት ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል፡፡

የተሻሻለው የምርጫ ሕግ ለአካባቢ ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል ምን ያህል ተወካዮች እንደሚመርጡ እንደየምርጫው ዓይነትና ለየምክር ቤቱ የሚመርጡትን አባላት መሠረት በማድረግ በየክልሎቹ ሕግ እንደሚወሰን ይደነግጋል፡፡ በምርጫ 97 የቀበሌ ምክር ቤት አባላት ቁጥር 15 የነበረ ሲሆን፣ ከ1999 ዓ.ም. ማሻሻያ በኋላ ግን አብዛኛዎቹ ክልሎች የቀበሌ የምክር ቤት ቁጥርን ወደ 300 ከፍ አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ዝቅተኛው ቁጥር 100 ከፍተኛው ደግሞ 300 እንደሚሆን በክልሉ ሕግ ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት በቀበሌና ወረዳ ምክር ቤቶች ምርጫ የሚሳተፍ አንድ ፖለቲካ ፓርቲ ለ3.6 ሚሊዮን ወንበሮች ዕጩዎች ማቅረብ አለበት፡፡ 

ከ70 በላይ ሕጋዊ ፓርቲዎች በሚገኙበት አገር በአካባቢ ምርጫ ድምፁ ጎልቶ የሚሰማውና ስሙ ደምቆ የሚታየው ፓርቲ (ግንባር) ኢሕአዴግ ብቻ ነበር፡፡ ዶ/ር ዘመላክ አየለ ‹‹Local Government in Ethiopia: Still an Apparatus of Control?›› በተሰኘ ሥራቸው፣ አቶ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ‹‹Tackling Abuse of Incumbency and the Imperial Premiership: Ideas for Constitutional Reform in Ethiopia›› በተሰኘ ሥራቸው የምክር ቤቶቹ የአባላት ቁጥር ማደግ ተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹን እንደሚያዳክም በማወቅ ኢሕአዴግ በስሌት የሕግ ማሻሻያውን እንዳደረገ ይከሳሉ፡፡ ይሁንና ሁለቱም ምሁራን ወቀሳው ለኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን ደካማ አደረጃጀትና አፈጻጸም ከማሳየት ወደ ኋላ ብለው የማያውቁት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፖለቲካ ተንታኝ ምርጫ ያለአማራጭ ፖለቲካ ፓርቲ ስሜት የሚሰጥ ነገር እንደማይሆን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ብቻውን ለሚወዳደርበት ምርጫ ውድ የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችንም በዕጩነት አቅርቧል፡፡ እርግጥ የሕዝብ ተወካይዋ ወ/ሮ አዜብ መስፍንን የጀመሩትን ዘመን ሳይጨርሱ በአካባቢ ምርጫ ማሳተፉ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ምርጫውን ‹‹ምርጫ›› ከማለት ይልቅ የመተማመኛ ድምፅ ማግኛ (vote of confidence) ቢባል ይቀለዋል፡፡ ክርክርና ውይይት ሊደረግባቸው የሚገቡ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በእያንዳንዱ አካባቢ ነበሩ፡፡ የውድድር ስሜት ስላልነበረ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልተደረጉም፤›› ብለዋል የፖለቲካ ተንታኙ፡፡ 

በተጨማሪም የፖለቲካ ተንታኙ የምርጫ ቦርድንና ሚዲያውን ተችተዋል፡፡ ‹‹ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም የሚለው ወቀሳ አሁንም አለ፡፡ የምርጫ ባህልን ለማጎልበት ወደ እያንዳንዳችን ቤት እየገባ መመዝገባችን ማረጋገጥና መምረጣችንን ማረጋገጥ አይጠበቅበትም፡፡ ምርጫ መብት እንጂ ግዴታ እንዳልሆነ ምርጫ ቦርድ ሊያውቅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡     

የግንዛቤ ችግር
ዜጎች የአካባቢ ምርጫን እንደቀላል ነገር እንዲያዩት በማድረግ በኩል ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠረው የአካባቢ አስተዳደር ሚና ላይ ያለው የግንዛቤ ችግር መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ከአሃዳዊ አስተዳደር ወደ ፌዴራላዊ አስተዳደር ለመሸጋገር በመሀል ባለፈችበት የሽግግር ጊዜ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣን አግኝተው ነበር፡፡ የ1983 ዓ.ም. የሽግግር ዘመቻ ቻርተር በአንቀጽ ሁለት ላይ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ማንነት የመጠበቅና የማስከበር፣ ባህሉንና ታሪኩን የማበልፀግ፣ እንዲሁም በቋንቋው የመጠቀምና ቋንቋውን የማሳደግ መብት እንዳለው፤ በራሱ የተወሰነ መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ የራሱን ጉዳይ በራሱ የማስተዳደር፣ እንዲሁም በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ በነፃነት፣ አድልዎ በሌለበትና ተገቢ በሆነ የውክልና አግባብ ውጤታማ ተሳትፎ የማድረግ መብት እንዳለው ተገልጾ ነበር፡፡ 

ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ‹‹Decentralization, Local Government and Federalism in Ethiopia›› በተሰኘ ሥራቸው የአካባቢ አስተዳደሮችን በተመለከተ ሁለት ነገሮችን በመለየት ረገድ የግንዛቤ ችግር እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በአንድ በኩል የአካባቢ አስተዳደሮች የማዕከላዊ መንግሥትን ዓላማ ለማስፈጸም የተቋቋሙ ቅርንጫፎች አድርጎ የማየት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢ አስተዳደሮች የተመረጡበትን አካባቢና የመራጮቹን ልዩ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያላቸው አካላት አድርጎ የማየት የግንዛቤ ችግር አለ፤›› ብለዋል፡፡ 

ዶ/ር ካሳሁን የአካባቢ አስተዳደሮች የሚሰጡዋቸው ሥራዎች በተሻለ ጥራትና ውጤታማነት በእነሱ የሚፈጸሙና ለአወቃቀራቸው የተመቹ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አዋጅ ቁጥር 7/84 የአካባቢ አስተዳደሮች የሥልጣን ምንጭ ምርጫ እንጂ ሹመትና ውክልና አለመሆኑን በመደንገግ ከላይ የተገለጸውን የግንዛቤ ችግር ቢያንስ በሽግግር ዘመኑ ጊዜ መቅረፉን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ሕጉ በግልጽ ይህን ቢያስቀምጥም ከደቡብ ክልል በስተቀር ከ1983 ዓ.ም. እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ የአካባቢ አስተዳደሮች ተመራጭ እንዳልነበሩና ምርጫ በተደረገባቸው ክልሎችም አስተዳደሮቹ ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለበላይ ምክር ቤቶች ጭምር እንደነበር ያስገነዝባሉ፡፡

ከ1993 ዓ.ም. በኋላ ግን ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ ከክልል መንግሥታት ወደ አካባቢ አስተዳደሮች መሸጋገሩን ዶ/ር ካሳሁን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በአራቱ ዋና ዋና ክልሎች በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የወረዳ አስተዳደሮችን የማጠናከር ዕርምጃ መወሰዱን የሚጠቁሙት ዶ/ር ካሳሁን፣ ያለቅድመ ሁኔታ ከበላይ አስተዳደሮች የገንዘብ ዝውውር መደረግ መጀመሩ፣ ከራሳቸው ገቢ ወጪ እንዳያደርጉ መፈቀዱና ተጨማሪ ገቢ እንዲፈጥሩ መበረታታቸው፣ ክህሎትና ልምድ ያለው የሰው ኃይል እየተመደበላቸው መምጣቱ፣ በጀት የማቀድና የማዘጋጀት ነፃነት ማግኘታቸውና የሚፈልጉትን ሠራተኛ የመቅጠር ሥልጣን ማግኘታቸው እንደተጨባጭ ማስረጃ የሚወሰዱ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ይሁንና ከላይ የተገለጸው የዶ/ር ዘመላክ አየለ ጥናት እንዲሁም ራሳቸው ዶ/ር ዘመላክ አየለ ከዶ/ር ዮናታን ፍስሐ ጋር በሠሩት ‹‹The Constitutional Status of Local Government in Federal System: The Case of Ethiopia›› በተሰኘ ሥራ ዶ/ር ካሳሁን ተለውጧል ያሉት የአካባቢ አስተዳደሮች የማዕከላዊና የክልል መንግሥታት መሣሪያና ቅርንጫፍ የመሆን ችግር አሁንም መቀጠሉን ያሳያል፡፡ ዶ/ር ዘመላክና ዶ/ር ዮናታን የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት እንደ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥቶች የአካባቢ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ደረጃ በግልጽ አለማስቀመጡ፣ አስተዳደሮቹ ካለባቸው የገንዘብ ችግርና በሁሉም የመንግሥት እርከኖች ከተንሰራፋው የአንድ ፓርቲ የበላይነት ጋር ተዳምሮ ነፃነት የተጎናፀፉ የአካባቢ አስተዳደሮችን በኢትዮጵያ መመሥረትን ከባድ ሥራ ማድረጉን ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱ ምሁራን አብዛኛዎቹ የክልል ሕገ መንግሥቶች የአካባቢ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ተግባራት አለመዘርዘራቸውንና የክልል ሕግ አውጪ አካላትም ክልላዊ ሕግ አለማውጣታቸውን ጠቁመው፣ የአካባቢ መስተዳድሮች ሥልጣንና ተግባር በአብዛኛው የመነጨው ከፖለቲካ ውሳኔዎች መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ 

የፌዴራል መንግሥት ጫና
የአካባቢ ምርጫ የሚገባውን ትኩረት እንዳያገኝ ያደረገው ሌላው አንኳር ምክንያት የፌዴራል መንግሥት በአካባቢ አስተዳደሮች ላይ የሚያሳርፈው አግባብነት የሌለው ተፅዕኖ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

የአካባቢ አስተዳደሮች ለሕዝቡ እጅግ የቀረቡና መጠነ ሰፊ የዜጎች ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተመቹ ናቸው፡፡ የተለያዩ ኅብረተሰብ አቀፍ መፍትሔዎችንና አማራጭ ሐሳቦችን በማፍለቅ ለፌዴራል ሥርዓቱ መሠረት የሚሆኑም አካላት ናቸው፡፡ ለአካባቢ ልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ መሣሪያም መሆን ይችላሉ፡፡ ዶ/ር ካሳሁን የአካባቢ አስተዳደሮች ለድህነት ቅነሳ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለመፍጠርና መልካም አስተዳደርን ለሰፊው ሕዝብ ለማስፈን የተመቹ መዋቅሮች መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡ 

ዶ/ር ዘመላክም በተመሳሳይ የመንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች በተለይም ከድህነት ቅነሳ ጋር የተያያዙት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ለማምጣት የአካባቢ አስተዳደሮች የሚኖራቸውን ጉልህ ሚና ማስቀመጣቸውን ይጠቅሳሉ፡፡  

አቶ ገብረ ሕይወት ባራኪ ‹‹The Making of States and Local Governments in the Multi – Ethnic Federation of Ethiopia›› በተሰኘ ሥራቸው የአካባቢ አስተዳደሮች በሚገባ ከተዋቀሩና ነፃነት ከተጎናፀፉ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንደሚያመጡ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን የአካባቢ አስተዳደሮች የተፈጠሩበት አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይና በቅርብ ዓመታት እየተደረጉ ያሉ የአካባቢ አስተዳደሮች አወቃቀር ለውጦችና ክለሳዎች ሲቃኙ፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በፖለቲካዊ ምክንያቶች እንደሚዋጡ ያስገነዝባሉ፡፡ እንደምሳሌም የደቡብ ክልል መሠረት ሆነ በክልሉ በተከታታይ የአካባቢ አስተዳደሮች ክለሳ ሲደረግ ባለድርሻዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ሳይመክሩበት ከፌዴራል መንግሥቱ በመጣ ጫና መፈጸሙን ይጠቅሳሉ፡፡ 

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀ 39(3) የሚከተለውን አስፍሯል፡፡ ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፡፡›› ሕገ መንግሥቱ ከሽግግር ቻርተሩ አንቀጽ 2 ጋር ተመሳሳይ የሆነውን አንቀጽ 39(3)ን ብቻ ሳይሆን አንቀጽ 50(4)ንም አቅፏል፡፡ አንቀጽ 50(4) ‹‹ክልሎች በክልልነትና ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኙዋቸው የአስተዳደር እርከኖች ይዋቀራሉ፡፡ ሕዝቡ በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች በቀጥታ ይሳተፍ ዘንድ ለዝቅተኛ እርከኖች በቂ ሥልጣን ይሰጣል፤›› ይላል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ የአካባቢ አስተዳደሮች ከልማትና ከኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ከላይ ከተገለጹት የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች አኳያ፣ ከፌዴራሉም ሆነ ከክልል መንግሥታት ነፃ ሆነው የመረጣቸውን ሕዝብ እንዲያገለግሉ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለባቸው ያስረዳሉ፡፡ 

ዶ/ር ዘመላክ አየለ የአካባቢ አስተዳደሮች ነፃ ሆነው የራሳቸውን ሥራ ከመሥራት ይልቅ ለፌዴራል መንግሥቱና ለገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የፖለቲካና የአስተዳደር ቅርንጫፎች በመሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደሚጨቁኑ፣ ለማዕከላዊ መንግሥቱም ነፃ ጉልበት በማዋጣትና ግብር በመሰብሰብ የቁጥጥር መሣሪያ እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ዶ/ር ዘመላክ ለዚህ ችግር ሦስት መንስዔዎችን ይጠቅሳሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት በክልሎችና በአካባቢ አስተዳደሮች መካከል ግልጽ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል አለመደረጉን ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የከተማ አስተዳደሮች በክልል ሕገ መንግሥቶች ሳይሆን በተራ የክልል ሕግ መቋቋማቸው በየጊዜው እንደገና እንዲዋቀሩ ማድረጉ ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት የአካባቢ አስተዳደሮች አሁንም በክልል መንግሥቱ ሥር እንዳለ አንድ መዋቅር እንጂ እንደ አንድ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር መዋቅር አለመታየታቸው ነው፡፡ 

የአካባቢ አስተዳደሮች የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩት የፖሊስና የደኅንነት ተቋማቸውን በማሰማራት፣ የስብሰባ አዳራሾችን በመከልከል፣ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት በመንፈግ፣ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ላይ ጫና በማድረግ መሆኑን ዶ/ር ዘመላክ ይጠቁማሉ፡፡ በተቃራኒ እነዚህ የመንግሥት መዋቅሮች የገዥው ፓርቲ ፕሮግራሞችን በማስተዋወቅና አባላትን በመመልመል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ዶ/ር ዘመላክ ያስረዳሉ፡፡ አቶ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ከላይ በተገለጸው ሥራቸው የአካባቢ አስተዳደሮች የመንግሥትን ሀብት ለገዥው ፓርቲ በማዋልና ሌሎች ፓርቲዎች በተመሳሳይ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በመከልከል በኢሕአዴግና በሌሎች ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እንዲመጣ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ቀድሞ ከኢሕአዴግ ይልቅ ተቃዋሚዎችን ይመርጡ የነበሩ ወጣቶችና የተማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ‹‹በካሮትና በዱላ››/በጥቅማ ጥቅምና በማስፈራራት ወደ ኢሕአዴግ ለመሳብ የአካባቢ አስተዳደሮች የመንግሥትን ሀብት መጠቀማቸውን አቶ ጌዲዮን ይጠቁማሉ፡፡ 

ዶ/ር ካሳሁን ኢሕአዴግ በተቃዋሚዎችና በተቺዎች የመንግሥትን ሥልጣን ለፓርቲ ሥራ ይጠቀማል በሚል እንደሚተች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እንደሚያዋክብና ጠንካራ ዕጩዎችን ከምርጫ ሒደቱ እንደሚያስተጓጉል፣ መራጮችን በተለያዬ ተፅዕኖ ሥር እንደሚጥል፣ የፓርቲውን ደጋፊዎች ከነፃና ተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ጋር በሚያደርጉት ውድድር ድጋፍ እንደሚያደርግ የተለያዩ ክሶች እንደሚቀርቡበት አስታውሰው፣ እነዚህ ነገሮች እውነትነት ካላቸው አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት እንደሚወስዱና የዲሞክራሲ ግንባታውንም እንደሚያቀጨው ይገልጻሉ፡፡ 
ኤለንና ትሮንቮል በ2000 ዓ.ም. የተካሄደውን የአካባቢ ምርጫ አስመልክተው በጻፉት ‹‹The 2008 Ethiopian Local Elections: The Return of Electoral Authoritarianism›› በተሰኘ ሥራቸው፣ የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትርና የያኔውን የኢሕአዴግ የምርጫ ኮሚቴ ሰብሳቢን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን አናግረው በምርጫ 97 የኢሕአዴግ አባላት ቁጥር 760,000 ብቻ እንደነበርና በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አራት ሚሊዮን ማደጉን እንደተረዱ ገልጸዋል፡፡ ኤለንና ትሮንቮል ኢሕአዴግ የፓርቲውን አባላት ቁጥር ለመጨመር የመንግሥት ተቀጣሪዎች ላይ ጫና መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ ኢሕአዴግ የአካባቢ አስተዳደሮችን ለመቆጣጠርና ሌሎች ፓርቲዎችን ለማዳከም በስፋት መሥራት የጀመረው ከምርጫ 97 በኋላ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ለፌዴራል መንግሥት በቀጥታ በጀት ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ በመሠረታዊ አገልግሎት አቅርቦት ፕሮግራም በኩል የአካባቢ አስተዳደሮች ዕርዳታውን ለተጠቃሚዎቹ በቀጥታ እንዲያደርሱ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ኢሕአዴግና የሚመራው የፌዴራል መንግሥት የአካባቢ አስተዳደሮች ነፃ መሆናቸውንና የስኬቱ መሠረትም ያስመዘገበው ውጤት እንደሆነ ይከራከራል፡፡ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ከድል የራቁት በስንፍናቸው መሆኑን አበክሮ ይናገራል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ኢሕአዴግ ለድሉ ምክንያት የሚያደርገው ያለው ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና የፓርቲው ፕሮግራሞች ተፈትነው አዋጪ በመሆናቸውና ፓርቲውም ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ተፈትኖ ያለፈ ፓርቲ መሆኑን በመግለጽ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ኤለንና ትሮንቮልም ኢሕአዴግ በአካባቢ ምርጫዎች ተወዳዳሪ ያጣው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተከፋፈሉና በሚገባ የተደራጁ ባለመሆናቸው እንደሆነ የሚያምን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ በረከት ስምኦንን በመግለጽም ተቃዋሚዎች የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ከምርጫ ራሳቸውን የሚያገሉት ሽንፈትን ለማምለጥ መሆኑን እንደሚያምን አስፍረዋል፡፡ 

የፖለቲካ ባህልና የፖለቲካ ፓርቲዎች ደካማ ይዞታ
በአስተያየት ሰጪዎቹ የተጠቀሰው ሌላኛው የአካባቢ ምርጫን ትኩረት የነፈገ ዋነኛ ምክንያት በአገሪቱ የፖለቲካ ባህል በሚገባ አለመስፈኑና በዚህም ኢሕአዴግን ጨምሮ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠያቂ መሆናቸውን ነው፡፡ የፖለቲካ ባህሉ ከ20 ዓመታት በኋላ አሁንም በማግለልና በመጠራጠር የተሞላ ሲሆን፣ አንዱ ፓርቲ ሌላውን ለማዳከምና ለማጥፋት በሚያደርገው ጥረት ሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ ውጪ የጎላ ተወዳዳሪ ፓርቲ ማየት አልተቻለም፡፡ 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ባለመዳበሩ የተነሳ ከሕዝቡ፣ ከመንግሥት፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ የሚጠብቁትን ያህል ድጋፍ አለማግኘታቸው ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና ፓርቲዎቹ አደረጃጀታቸውን በማስተካከል ሕዝቡን የማንቀሳቀስና ውጤታማ የመሆን ሥራ እየሠሩ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ያላቸውን አቋም እንኳን የሚተነትን ፕሮግራም የሌላቸውና አመራራቸውም ፖለቲካን እንደ ትርፍ ጊዜ ሥራ በያዘበት ሁኔታ እጅግ የፈረጠመውን ኢሕአዴግን ለመወዳደርና አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ አዳጋች ነው፡፡ ዶ/ር ዘመላክ የኢዴፓውን ልደቱ አያሌውን በመጥቀስ አብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ለአካባቢ ምርጫ ባለው ዝቅተኛ ግምት የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ዘመላክ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአካባቢ አስተዳደር ውስጥ ተወካይ እንደሌላቸውና መራጮችን የሚስብ ፕሮግራም ባለቤት እንዳልሆኑም ገልጸዋል፡፡ ይሁንና እንደ ዶ/ር ዘመላክ ዕይታ ተቃዋሚዎች አስፈላጊነቱን ያልተገነዘቡት የአካባቢ አስተዳደር የተቃዋሚዎችን ዕድገት ግን እየገታ ነው፡፡ 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ እንደ ኢሕአዴግ ያሉ ጠንካራ ፓርቲዎችን በህንድና በሜክሲኮ ለማሸነፍ ጥረቱ የተጀመረው ከአካባቢ ምርጫ እንደነበር አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ግን ትኩረታቸው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ብቻ መሆኑን ተችተዋል፡፡ ‹‹ምናልባት በነፃነት እንዳይሠሩ ጫና ይኖርባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለአካባቢ ምርጫ ዕጩ አጥተው ከምርጫ ራስን ማግለል በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህን መሠረታዊ ችግር መፍታት ካልቻሉ ፈቃዳቸውን ይመልሱና ራሳቸውን ይዝጉ፡፡ ምናልባት የእነሱን ስህተት የማይደግም አዲስ ፓርቲ ይመጣ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡    

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር