በዎንሾ ወረዳ በህብረተሰብ ተሣትፎ የተለያዩ የትምህርት ልማት ስራዎች ተከናወኑ

አዋሳ ሚያዚያ 29/2005 በሲዳማ ዞን የዎንሾ ወረዳ አንድ ሚሊዮን ብር በሚገመት የህብረተሰቡ ተሣትፎ የተለያዩ የትምህርት ልማት ስራዎች መከናወናቸውን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሰማ ተፈራ ሰሞኑን እንደገለጹት በህብረተሰቡ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ከተሰሩት የትምህርት ልማት ስራዎች መካከል አራት አዳዲስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 52 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም 50 ነባር የመማሪያ ክፍሎች፣ ስምንት ቤተመጻህፍት፣ አምስት ቤተ ሙከራዎችና ከአንድ ሺህ በላይ ወንበሮች ዕድሳትና ጥገና ከመደረጉም በላይ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግና የማስፋፋት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡ ስድስቱን የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጆችን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ከማድረግ አንፃርም የትምህርት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተማሪውን ውጤት ለማሻሻልም በየሳምነቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ አመልክተው በአንድ ለአምስት ቁርኝትና በትምህርት ልማት ሰራዊት በማደራጀት በውጤት ደከም ያሉትን የመደገፍና ክትትል የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ ባለፈው የትምህርት ዘመን በ8ኛ፣ በ9ኛና በ10ኛ ክፍሎች በአማካኝ 65 በመቶ ማሳለፍ መቻላቸውን ጠቁመው ዘንድሮ 90 በመቶ ለማሳለፍ እቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመምህራን በኩልም የሚስተዋሉ ክፍተቶችና የሚደግሙና የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ በየትምህርት ክፍሉ፣ በክበባትና በተማሪዎች ፓርላማ በመታገዝ ወቅታዊ ግምገማና ክትትል ስለሚደረግ ክፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው የወረዳው ትምህርት ጥራትና ደራሽነት ለማስጠበቅ በተደረገው ጥረት ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ተማሪዎች በሳይንስና ቴከኖሎጂ ዕውቀት እንዲካኑ ፣ ለትምሀርት ቤቶች መስፋፋት ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋሉ ማለታቸውን የዞኑ ባህል ፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ባለፈው ሀሙስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=7688

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር