የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የህብረተሰብ አገልግሎትን ለማጠናከር እየሰራ ነው ይላል

አዋሳ ግንቦት 22/2005 የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ አገልግሎትን እንደ መደበኛ ፕሮግራሙ በማቀፍ የምርምር ውጤቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ስራውን አሰፋፍቶና አጠናክሮ መቀጠሉን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ገለጹ፡፡ ዩኒቨርስቲው ለስራ አጥ ወጣቶችና ሴቶች በዘመናዊ የዶሮ እርባታ ዙሪያ ያዘጋጀው ስልጠና ትናንት በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡ ስልጠናውን የከፈቱት የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት የመማር ማስተማር ስራቸውን ከምርምር ጋር አቀናጅተው ያገኟቸውን አዳዲስና ችግር ፈቺ ውጤቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ስድስት የቴክኖሎጂ መንደሮች ተቋቁመዋል፡፡ የህብረተሰብ አገልግሎትን እንደ መደበኛ ፕሮግራማቸው በማቀፍ በምርምር የተገኙ የግብርና፣ የጤናና ሌሎችን ውጤቶችን በተለይ ስራ አጥ ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የመስሪያ ግብአቶችን በማሟላት ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ ብቻ በደን ልማትና ችግኝ እንዲሁም በእንጉዳይ አመራረትና አጠቃቀም ላይ ከሀዋሳ ከተማና ከሲዳማ ዞን ሁላ ወረዳ ለተወጣጡ በርካታ ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አመልክተው አሁንም ለ24 ወጣቶች በዘመናዊ የዶሮ እርባታ ዙሪያ ስልጠና አዘጋጅተው እራሳቸውን ችለው በተመሳሳይ ለሌሎችም የሚበቁበት የአቅም ግንባታ ድጋፍ አያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን እናበረታታለን ያሉት ዶክተር ዮሴፍ ዩኒቨርስቲው አጠቃላይ የትምህርት ተቋም እንደመሆኑ ሌሎችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የምርምር ውጤቶችን ለህብረተሰቡ በማሸጋገር ተጠቃሚ ለማድረግ ስራቸውን በሁለገብነት አስፋፍተውና አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የምርምርና ልማት ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ አበበ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ማድረግ እያካሄዱት ካሉት ምርምሮች መካከል በአሁኑ ወቅት የ38 ፕሮጀክቶች ጥናት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ እነዚህም በግብርና፣ በተፈጥሮ ሀብትና ደን ልማት፣ በእንስሳት፣ በጤና ፣ በትምህርትና ሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በምርምር የተገኙት የተሻሉና ችግር ፈቺ ውጤቶችን ለህብረተሰቡ ለማዳረስና ለማስፋፋት ባቋቋሟቸው የቴክኖሎጂ መንደሮች በኩል በማስተዋወቅ እየሰሩ ናቸው፡፡ ዘንድሮ ብቻ በደንና በእንጉዳይ ልማት ላይ ከሀዋሳ ከተማና ከሲዳማ ዞን ሁላ ወረዳ ለተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶችን በማሰልጠንና የመስሪያ ቁሳቁስ አሟልተውላቸው ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ለአራት ቀናት በተዘጋጀው ስልጠና ላይ ለተሳተፉት 24 ወጣቶችና ሴቶች ስለ ዶሮ ቤትና መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የዶሮ መኖና አመጋገብ፣ የዶሮ በሽታና መከላከያ መንገዶች ዙሪያ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በባለሙያዎች ይሰጣል፡፡ የሚሰሩበት የዶሮ ቤትና መኖ ቀደም ብሎ ከመመቻቸቱም በላይ ምርጥ የዶሮ ዝርያዎች እንደሚሰጣቸውን ዶክተር ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ 250 የምርምር ፕሮጀክቶች እያካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አምስት ካምፓሶችን በስሩ በማስተዳደር 31 ሺህ ተማሪዎችን በ64 የትምህርት ዘርፎች የመጀመሪያ ዲግሪና በ43 የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች እያሰለጠነ እንደሚገኝ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ተናግረዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=8314&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር