የምርት ገበያው ደካማ አሠራር ቡና አቅራቢውን እያኮላሸው መሆኑ ተገለጸ


የምርት ገበያው ደካማ አሠራር ቡና አቅራቢውን እያኮላሸው መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አሠራር ችግር እየፈጠረባቸውና ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን የቡና አቅራቢዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለይ የሲዳማ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡
ማኅበሩ በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ባካሄደው ስብሰባ፣ በሐዋሳ የሚገኘው የምርት ገበያው ማዕከል፣ አደረሰብን ያሉትን ችግር በዝርዝር በማስቀመጥ፣ ይህንን ችግር እንዲፈታላቸው ለመንግሥት አቤት ብለዋል፡፡ 
በስብሰባው ወቅት እንደተገለጸውና መንግሥት እንዲያውቅልን በማለት በጽሑፍ ያዘጋጁት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ችግሩ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ የተዛባ የቡና ጥራት ደረጃ አሰጣጥን የሚያጠቃልል ነው፡፡
የቡና ደረጃ አሰጣጥ ላይ ያለው የተዘበራረቀ አሠራር ከአቅማችን በላይ ሆኗል የሚሉት የማኅበሩ አባላት፣ ደረጃውን ጠብቆ የተዘጋጀ ቡና በአንዱ የምርት ገበያው ማዕከል ባለሙያዎች የተሰጠው ደረጃ በሌሎች ማዕከሎች ግን ደረጃውን አልጠበቀም ተብሎ ይጣልባቸዋል፡፡ 
ባለፉት ሁለት ወራት የሐዋሳው የምርት ገበያ መጋዘን ጥበት አጋጥሞታል በመባሉ ወደ አዲስ አበባ የላኩት ቡና፣ ሐዋሳ ላይ ደረጃ አምስት ተብሎ አዲስ አበባ ላይ ግን በጥራቱ የደረጃ ሁለት ማዕረግ እንደተሰጠ የተመደበ ሲሆን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ 
እንዲህ ባሉ አግባብ ያልሆኑ አሠራሮች ምክንያት የቡና ላኪዎች ጉዳት ላይ እየወደቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ችግር አንድ ቡና አቅራቢ ድርጅት በአንድ መኪና በግምት ከ80 እስከ 100 ሺሕ ብር እየከሰረ ይገኛል ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሐዋሳ የሚገኘው ምርት ገበያ፣ ቡናቸውን ለኤክስፖርት ገበያ መቅረብ የማይችል  (Undrscreen) በማለት ከገበያ ውጪ ሲያደርገው በተደጋጋሚ የሚከሰት ድርጊት በመሆኑ፣ እንደዚህ ያለና ሁሌም ጥራት የማይኖረው ቡና ሊኖር አይችልም በማለት የሚያሰሙት አቤቱታ ግን ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ የምርት ገበያ የሚጠቀምበት የጆንያ መውጊያ (መመርመርያ) ቡናዎቹን ከሚገባው በላይ የሚያፈስ ከመሆኑ አንጻር በርካቶቹ የቡና ምርቶች ለገበያ መቅረብ የማይችሉ ተብለው የሚጣሉ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ 
አባላቱ አክለውም፣ እነዚህን የቡና ምርቶች ገበያ መቅረብ የማይችሉ፣ የወረደ ጥራት ያላቸው ብለው በዝቅተኛ ዋጋ ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲሸጡ መገደዳቸውን በስብሰባቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ ለውጭ ገበያ መቅረብ አይችልም የተባለውን ምርት ግን ላኪዎች ተሯሩጠው እንደሚገዙት፣ ይህንንም በማስረጃ ማረጋገጥ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ የማኅበሩ አባላት ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ በርካቶቹ የቡና ምርቶች ለውጭ ገበያ የማይቀርቡ ናቸው እየተባልን ላኪዎች ግን በጐን የሚገዙት ከሆነ የጥራት ማረጋገጫውን እንድንጠራጠረው ያደርገናል ብለዋል፡፡ 
ለዚህ ጥርጣሬያቸው ማስረጃ ብለው ካቀረቡት መካከል ሐዋሳ ላይ ለውጭ ገበያ መቅረብ አይችልም ተብሎ የነበረው ቡና፣ በተመሳሳይ ጊዜ ከአንድ መጋዘን በአራት መኪና ላይ ከተጫነ ተመሳሳይ ቡና ውስጥ የሁለቱ መኪና፣ ልዩ ቡና (Speciality Coffee) የሚል ደረጃ ሲወጣለት፣ በሁለቱ መኪና የተጫነው ደግሞ ደረጃ ሦስት ተብሏል፡፡ 
እንዲህ ያሉ አሠራሮች ሲታዩ በሐዋሳው እና በአዲስ አበባው የምርት ገበያ የጣዕም ልኬትና የደረጃ አሰጣጥ ልዩነት መኖሩን የሚያረጋግጡ በመሆኑ እንዲህ ያሉት ክፍተቶች በአግባቡ እንዲታዩላቸው ጠይቀዋል፡፡ 
በተጨማሪም ሐዋሳ ላይ ቡና አቅራቢው የቡና መያዣውን ጆንያ ገዝቶ ለላኪው ያለምንም ክፍያ ያስተላልፋል ያሉት አቅራቢዎቹ፣ ይሁንና ላኪው ይህንኑ ጆንያ መልሶ ለእነሱ በተደጋጋሚ መሸጥ የሚችልበት ክፍተት ለቡና አቅራቢው የተመቸ አለመሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እንዲህ ባለው አሠራር ለአንድ መኪና ብቻ 5,760 ብር ወጪ እናደርጋለን፣ ይህ ወጪ ለእኛ የሚቀርልን ባይሆንም፣ ያለ አግባብ ለአንድ ጆንያ በተደጋጋሚ ክፍያ እንፈጽማለን፤›› ብለዋል፡፡ 
የሲዳማ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተመሠረተባቸው ዓላማዎች ሙሉ ለሙሉ በተግባር ላይ አልዋሉም በማለት በስብሰባቸው ወቅት አፅንዖት ከሰጡባቸው ክስተቶች መካከል፣ ትርፍም ይሁን ኪሳራ ሲመጣ ሙሉ በሙሉ የሚመለከተው አካል ማለትም የቡና ባለቤት በመሆኑ፣ በግብይት ሒደት ወቅትም ወሳኝ ሆኖ ግብይቱ እንዲካሄድ ጠይቀዋል፡፡ 
ቡና ገዢዎች ከሌሎች የግብይት ተዋናዮች ጋር በመመሳጠር ከምርት ገበያ መገበያያ ቦታ ውጪ ተደራድረው ዋጋ የሚወስኑበት አካሄድ እንዳይኖር፣ እንዲሁም የማንኛውም ምርት /ቡናን/ ጨምሮ የጥቅም ፍሰቱ አምራቹን በማይጐዳ እውነታ ላይ ብቻ እንዲመሠረት ጠይቀዋል፡፡ 
ከዚህም ሌላ ያለ ሥራው፣ ያለድካሙ፣ ለመንግሥት ግብር የማይከፍል አካል ተጠቃሚ የሚሆንበት አሠራር መወገድ የሚኖርበት መሆኑን ያስገነዘቡት እኒሁ ቡና አቅራቢዎች፣ ከምንጊዜም በላይ በምርት ጥራትና ብዛት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ማድረግ ይኖርብናል በማለት ስምምነት አድርገዋል፡፡
በዕለቱ በተስማሙባቸው ነጥቦች መሠረት የቡና ባለቤት መቶ በመቶ ትርፍም ይሁን ኪሳራ ሲመጣበት፣ የሚመለከተው ክፍል ለምሳሌ ቡና አቅራቢ ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ካቀረበ በኋላ ምርቱን ከገዥ ጋር ፊት ለፊት በዋጋ ተደራድሮ የመሸጥ ዕድል የሌለው በመሆኑ ያ እንዲለወጥ ጠይቀዋል፡፡ 
ይልቁንም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውስጥ አባል በመወከል ብቻ ቡናውን መሸጥ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛው አባል ወንበሩን በከፍተኛ ዋጋ በጨረታ ያሸነፉና የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ያላቸው ቢሆኑም፣ የቡና አቅራቢዎችን እንዲወክሏቸው ይደረጋል፤ ራሳቸው ከመሸጥ ይልቅ በሌላ ሦስተኛ ወገን በኩል ለመሸጥ ይገደዳሉ፡፡ ለግለሰቦች የገበያ ሕጉ ውክልና ስለሚፈቅድላቸው ለባለወንበሮች ውክልና በመስጠት ሽያጩ ይከናወናል፡፡ 
በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቡና አቅራቢው ያቀረበው ቡና፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አባል ወይም በወኪል በኩል ብቻ ሽያጭ ላይ ስለሚውል፤ እንደዚሁም በተወሳሰበና አቅራቢው በማያውቀው ሦስተኛ ወገን በኩል ቡናው መሸጡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አሠራር ላይ ቡና አቅራቢዎች እምነት እንዲያጡ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡ 
በመሆኑም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አባል ወኪል (የመድረክ ሠራተኛ)፣ ከቡና አቅራቢው ጋር ፍጹም አለመተዋወቅ እንዳለ ሆኖ፣ የምርት ገበያው አባል ወይም ወኪል የቡና አቅራቢውን መረጃ ለቡና ገዥ (ላኪ) አስቀድሞ በመስጠት ችግር እየተፈጠረ ነው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ግብይት የሚፈቀደው 30 ቀን ግዥ ሳይፈጸም እየተጠናቀቀ መሆኑን ለገዥ አስቀድሞ መረጃ ይሰጥበታል፡፡ ቡና አቅራቢው በምርት ገበያው የተቀመጠው የሚጣልበትን የመገበያያ ቀን ካለቀ ቅጣት በመሸሽ፣ ቡናውን በዝቅተኛ ዋጋ ሳይወድ በግድ እንዲሸጥ ተፅዕኖ በመፍጠር ትልቅ በደል ይፈጸማል፡፡ 
የራሳቸውን የመግባቢያ ጥሪ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ገዥዎች፣ አምስት ቀን የቀረው (ይህም ግብይት መፈጸሚያው ቀን 25 ቀን በማለፉ) ቡና አቅራቢው ዋጋ አውርዶ እንዲሸጥ እያስገደዱት እንደሚገኙ አቅራቢዎቹ አማርረዋል፡፡  
ይህ ሁሉ ተደማምሮ ቡና አቅራቢዎች ሽያጭ ላይ በራሳችን ሥልጣን የመደራደር አቅም የሌለን በመሆኑና በምርት ገበያ አባል በኩል ግብይቱ የሚወሰን በመሆኑ፣ ቡና አቅራቢው በራሱ ንብረት ላይ ሙሉ በሙሉ መወሰን ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 
በዕለቱ አባላቱ ያነሱት ሌላው ነጥብ፣ የቡና ናሙና መውሰጃና የቡና ደረጃን የተመለከተው ይገኝበታል፡፡ 
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተቋቋመ በኋላም ሆነ ከመቋቋሙ በፊት፣ የቡና ናሙና መውሰጃ ሒደቱ አንድ ዓይነት እንደነበር በማስታወስ፣ በወቅቱ የነበረው የቡና ምርት ናሙና መውሰጃ በቡና አቅራቢም ሆነ ላኪ ላይ ያስከተለው ችግር አልነበረም ይላሉ፡፡ አሁን ግን ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በተለይ ከ2004 ዓ.ም. በፊት የነበረው የቡና ናሙና መውሰጃ ሥርዓት መልሶ ሥራ ላይ እንዲውል ተጠይቆ የተመለሰ ቢሆንም፣ በዚህ በያዝነው ዓመት ይሄው ‹‹ስታንዳርድ›› የሚባለውና ምርት ገበያው የሚጠቀምበት የቡና ናሙና መውሰጃ፣ በማይታወቅ ምክንያት እንደገና መጥቷል፡፡ ይህ በመሆኑም የቡና አቅራቢው የሚያቀርበው ቡና አብዛኛው ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችል ነው እየተባለ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን አቅራቢዎቹ አስታውቀዋል፡፡ 
ቡና አቅራቢያዎቹ እየተፈጸመብን ነው ያሉትን ተፅዕኖ በተመለከተ የምርት ገበያውን ኃላፊዎች ለማነጋገር በተደጋጋማ ያደረግነው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ኃላፊዎቹ ስለጉዳዩ ቀጥተኛ ማብራርያና ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር በጉዳዩ ምላሽ ነፍገዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር