ልቅሶ የተካው የእልልታ ቀን


‹‹የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ቅነሳ በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2015 እናሳካዋለን ያልነውን የሚሌኒየሙን ግብ አሁን በያዝነው አሠራር የምንቀጥል ከሆነ ግቡ ጋር ለመድረስ ተጨማሪ 150 ዓመት ያስፈልገናል፡፡›› ይህንን የተናገሩት የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) የኦፕሬሽን ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ኃይሉ ተስፋዬ ናቸው፡፡
ሁለት ዓመት ከሰባት ወር ገደማ ከቀረው ከሚሌኒየሙ እቅዶች መካከል አንዱ የሕፃናትና የእናቶች ሞት ቅነሳ ነው፡፡ ዶክተር ኃይሉም ግቡን ለማሳካት አሠራሮች ይቀየሩ የሚለውን ሐሳባቸውን ያንፀባረቁት፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሑድ በሐዋሳ ከተማ በተደረገው የ‹‹ሁሉም›› የእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳ ዘመቻ ላይ ነው፡፡ 
እ.ኤ.አ በ2015 ይሳካል የተባለለት ትልቁ ዕቅድ ጨቅላ ሕፃናት በተወለዱ በ24 ሰዓታትና በተወለዱ በመጀመርያዎቹ ሰባት ቀናት ውስጥ ተገቢው ክትትል ካልተደረገላቸው መሞታቸው ቀጥሎ ግቡም አይሳካም፡፡ በዚህ አሠራር ከተቀጠለ ግን ግቡን ለማሳካት እ.ኤ.አ 2165 ድረስ መቆየት ግድ እንደሚል ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡  የእናቶችን ሞት መቀነስን በተመለከተ ደግሞ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የእርግዝና ክትትል፣ የወሊድና ከወሊድ በኋላ የሚደረግ ክትትልና እንክብካቤ ከመቼውም በላይ የሚሠራባቸው ከሆነ የሚሌኒየሙን ግብ ማሳካት እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
የ‹‹ሁሉም›› ዘመቻ የእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳን ለማሳካት በዘመቻ መልኩ በሕፃናት አድን ድርጅት ሥር ከተመሠረተ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ በ36 አገሮች በየዓመቱ እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ዘመቻ፣ የእናቶችና ሕፃናት ሞት የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ማኅበረሰቡን በዘመቻው አነሳስቶ የሞቱን ቅነሳ ለማድረግ ጥረት የሚደረግበት ፕሮግራም ነው፡፡  
የሕፃናት አድን ድርጅት በየዓመቱ በዓለም ላይ ስላሉ እናቶች ያለውን ሁኔታ የሚያወጣበት ሪፖርት አለው፡፡ ዶክተር ኃይሉ 14ኛውን ሪፖርት ጠቅሰው እንደተናገሩት ከሆነ፣ በዓለም ላይ ዕድሜያቸው ከአንድ ወር በታች የሆኑ ሦስት ሚሊዮን ጨቅላዎች በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ለሞት የሚዳረጉት በተወለዱ የ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የተቀሩት ሁለት ሚሊዮን ሕፃናት ደግሞ በአጭር የሚቀጩት ከተወለዱ እስከ ሰባት ባሉት ተከታታይ ቀናት ውስጥ ነው፡፡ 
‹‹በየቀኑ ወደ 19 ሺሕ የሚጠጉ እናቶች እንደወለዱ ልጆቻቸው ይሞቱባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ወደ ስድስት ሺሕ የሚሆኑት በተወለዱ በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ የሚሞቱ ናቸው፤›› ያሉት ዶክተር ኃይሉ፣ ለጨቅላ ሕፃናት የመጀመርያዎቹ 24 ሰዓታት፣ የመጀመርያዎቹ ሰባት ቀናትና አራት ሳምንታት በሕይወት ለመቀጠል ፈታኝ ወቅቶች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ 
ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ የሕፃናት ሞትን መቀነስ በተመለከተ ባለፉት ሁለት አሠርታት ውስጥ ወደ 40 በመቶ መቀነስ እንደተቻለና የእናቶችን ሞት ደግሞ 50 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ ዶክተር ኃይሉ አስታውሰዋል፡፡ ቢሆንም ግን ዕድሜያቸው ከአንድ ወር በታች የሆነ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን መቀነስ በተመለከተ ውጤቱ እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 
የጨቅላ ሕፃናቱ ሞት 65 በመቶው የሚከሰተው አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ፡፡ ከእነዚህም መካከል ችግሩ የሚከፋው አሥር አገሮች ውስጥ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ 
የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑትና በዘመቻው ከታደሙት ተቋሞች መካከል የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አንዱ ነበር፡፡ የድርጅቱ የቻይልድ ሰርቫይቫል ፕሮግራም የጤና ሴፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ተድባብ ድጋፌ እንደተናገሩት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከሚወለዱ 1000 ሕፃናት ውስጥ 88ቱ ይሞታሉ፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ የሚሞቱት የጨቅላዎች ቁጥር ደግሞ 37 ነው፡፡
‹‹ከተወለዱ ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚገኙ የሕፃናት ሞት በየዓመቱ 5.5 በመቶ እየቀነሰ ነው፡፡ የጨቅላ ሕፃናት ሞት ደግሞ በ2.4 በመቶ በየዓመቱ እየቀነሰ ነው፡፡ ከተወለዱበት ቀን አንስቶ እስከ ስድስተኛው ቀን ድረስ የቆዩ ሕፃናት ሞት ደግሞ በየዓመቱ እየቀነሰ ያለው አንድ በመቶ ብቻ ነው፤›› ያሉት ዶክተሯ፣ የወሊድ ቀን ‹‹እልል›› የሚባልበት ቀን መሆኑ ለብዙ እናቶች ህልም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 
የሟች ጨቅላ ሕፃናት ቤተሰቦች ተወልዶ የሚያለቅስን ሕፃን ታቅፈው እልል ከማለት ይልቅ ሕፃናቶቻቸውን መቅበር ዕድል ፈንታቸው ሆኗል የሚሉት ዶክተር ተድባብ፣ ጨቅላዎቹ የሚቀጠፉበትን የጤናን እክል ሕክምና 90 በመቶ ለሚሆኑ እናቶች ማድረስ ቢቻል 67 በመቶ የሚሆነውን የጨቅላ ሕፃናትን ሞት መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡ 
ጨቅላዎቹ እንዲህ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ለሕይወታቸው መቀጠፍ ምክንያት የሆኑት ነጥቦች ሦስት ሲሆኑ፣ እነርሱም የሕፃናቱ ያለዕድሜ መወለድ፣ በወሊድ ጊዜ የሚፈጠር ችግርና በወሊድ ጊዜ የሰውነት በኢንፌክሽን መበረዝ ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት እክሎች 80 በመቶ የሚሆኑትን ሕፃናት እየገደሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ችግሮች የሚታከሙባቸው መንገዶች ዋጋቸው ቀላል ከመሆኑም ባሻገር ኅብረተሰቡ ጋር በቀላሉ መድረስ እንደሚችሉ ዶክተር ኃይሉ ገልጸዋል፡፡ 
‹‹ሕክምናውን በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ሞክረን ውጤታማ በመሆኑ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሕክምናው በሌሎች አካባቢዎች ለመስጠት በስፋት እየሠራ ነው፡፡ እነዚህ የሕክምና መንገዶች በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ጨቅላዎቹን ከሞት የሚታደጉ መሆናቸው ተረጋግጧል፤›› ያሉት ዶክተር ኃይሉ፣ እነዚህን የሕክምና መንገዶች ኢትዮጵያ በጥብቅ የምትከተል ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጨቅላዎቹን ሕይወት ከመታደግ አልፎ የሚሌኒየሙን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ተስፋ ሰጥተዋል፡፡ 
ይህ ከሆነ በልቅሶ የተተኩት የእልልታ ቀኖች የሚገባቸውን እልልታ ያስተናግዱና በአጭር የሚቀጠፈው ትውልድ በሕይወት ይቀጥላል፡፡     

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር