የሐዋሳውን ግማሽ ማራቶን ታምራት ቶላና ጽጌረዳ ግርማ አሸነፉ


ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ሴቭ ዘችልድረን አዘጋጅነት በሐዋሳ በተደረገው ግማሽ ማራቶን ውድድር፣ ታምራት ቶላ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸንፏል፡፡ በሴቶች በተደረገው ውድድርም ጽጌረዳ ግርማ በተመሳሳይ ክብረ ወሰኑን በማሻሻል ባለድል ሆናለች፡፡ 
“የሕፃናትንና እናቶችን ሞት ለመቀነስ” በሚል መሪ ቃል ባለፈው እሑድ በሐዋሳ በተደረገው ግማሽ ማራቶን ሩጫ የውድድሩ አሸናፊ ታምራት ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ 1 ሰዓት፣ 02 ደቂቃ 44 ሰከንድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የቦታውን ክብረ ወሰን በአንድ ደቂቃ አሻሽሎ መሆኑም ታውቋል፡፡ እሱን ተከትሎ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሐብታሙ አሰፋ 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 12 ሰከንድ ራሱ አምና ከተመዘገበው ሰዓት 26 ሰከንድ የተሻሻለ ሰዓት ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ ሦስተኛ የወጣው አስቻለው ንጉሤ በበኩሉ፣ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 20 ሰከንድ ሲሆን፣ ይህም ለአትሌቱ ፈጣን ሰዓት ተብሎለታል፡፡ 
በሴቶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር አሸናፊዋ ጽጌረዳ ግርማ የገባችበት ሰዓት 1 ሰዓት 13 ደቂቃ 19 ሰከንድ ከአምናው በ12 ሰከንድ ተሻሽሎ የተመዘገበ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ 
ውድድሩን ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቁት ጫልቱ ጣፋ 1 ሰዓት 14 ደቂቃ፣ 01 ሰከንድ፣ ቀነኒ አሰፋ ደግሞ 1 ሰዓት፣ 14 ደቂቃ 04 ሰከንድ መሆኑም ታውቋል፡፡ 
ለታላላቅ አትሌቶች መገኛ መሆኑ የሚነገርለት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ በሐዋሳ ከተማ በተደረገው ውድድር አትሌቶች ያስመዘገቡት ሰዓት በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ዕውቅና ካላቸው የውድድር ቦታዎች አንዱ ስለመሆኑ ጭምር ዝግጅት ክፍሉ አስታውቋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር