በሲዳማ ዞን ዘንደሮ ከ17 ሺህ 600 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀረበ

አዋሳ ግንቦት 05/2005 በሲዳማ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ17 ሺህ 600 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ግብይትና ህብረት ስራ መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የግብርና ግብይት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገነነ ገቢባ ባለፈው ቅዳሜ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዞኑ ቡና አምራች ከሆኑ 13 ወረዳዎች የቀረበው ይሄው ቡና በዘጠኝ ወሩ ተሰብስቦ ከተዘጋጀው 22 ሺህ 851 ቶን የታጠበ ቡና ውስጥ ነው፡፡ ቀሪው 5 ሺህ 245 ቶን የታጠበ ቡና በየወረዳዎቹ በመጋዘን በክምችት እንደሚገኝና በቅርቡ በተመሳሳይ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ከ95 በመቶ በላይ የታጠቡ ቡና መሆኑን አስተባባሪው አመልክተው ያለፉት ዘጠኝ ወራት አቅርቦት ከዕቅዱ ቢያንስም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጻር በ2 ሺህ 154 ቶን ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ከዕቅዱ አንጻር አቅርቦቱ የቀነሰው የአለም ገበያ ዋጋ መውረድ ጋር ተያይዞ ይጨምራል በሚል የመጠበቅና በክምችት የመያዝ ሁኔታ ቢስተዋልም አሁን የገበያው ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ በቀጠዩ ጊዜያት አቅርቦቱም ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ቡናው ተዘጋጅቶ ለማዕከላዊ ገበያ የተላከው በ51 የህብረት ስራ ማህበራትና በ244 የግል ባለሀብቶች አማካኝነት ነው፡፡ በቡና ማጠብና ዝግጅቱ ላይ 336 ኢንዱስትሪዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ቡና አምራች በሆኑት ወረዳዎች በእሻት ቡና ዝግጅትና አሰባሰብ ላይ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ51 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡ በእሸት ቡና ግዥ ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ዘንድሮ ከ923 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በደላሎች አማካኝነት የሚካሄድን ህገ ወጥ የቡና ንግድን ለመከላከል በተለይም የእሸት ቡና ግዥ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በዲፕሎማና በድግሪ የተመረቁ 1 ሺህ 471 ወጣቶችን በመቅጠርና ስርዓት በማስያዝ ገበያውን ለማረጋጋት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በበጀት አመቱ በአጠቃላይ 30 ሺህ 685 ቶን የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስተባባሪው ጨምረው ገልጸዋል፡፡\
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=7870&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር