በአንድ ቀን 14 ሠርግ ያስተናገደው ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል አሁን ባለ 5 ኮከብ ሆነ

ባለ 17 ፎቅ ሕንፃ የእንስሳት ማቆያ ዙና ሪዞርት እያሰቡ ነው
እንኳን ንግድ ገበያ ወጥተው የማያውቁ የተሟላ ትዳር የነበራቸው የቤት እመቤት ነበሩ፡፡ ባለቤታቸው ወታደር ስለነበሩ፣ መኖሪያቸው ካምፕ ውስጥ ነበር፡፡ የትዳር ጓደኛቸውን ሞት ሲወስድባቸው የሚይዙትንና የሚሆኑትን አጡ፤ ሰማይ የተደፋባቸው፣ ምድር የከዳቸው ያህል ክው አሉ፡፡ ቤት ውስጥ ምንም ስላልነበር፣ በላይ በላይ የተወለዱ አምስት ሕፃናት ያለ አባት ማሳደግ እጅግ ከብዶ ታያቸው፡፡ “ምኔን አብልቼ ነው የማሳድጋቸው? እንደፈለጋቸው ይሁኑ፤” … ብለው ሜዳ ላይ በትነዋቸው አልጠፉም፡፡ ለልጆቻቸው ያሏቸው ብቸኛ ወላጅ እሳቸው ብቻ ስለሆኑ እንደምንም ለማሳደግ ወሰኑ፡፡ ባለቤታቸው በሕይወት እያሉ ለቤተሰቡ ቀለብ የተሸመተ 25 ኪሎ ዱቄት ነበር፡፡ “ይኼ ዱቄት ካለቀ ልጆቼን ምን ላቃምሳቸው ነው? አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ” ብለው አሰቡ፡፡
ያቺን ዱቄት እየጋገሩ ሽሮ ወጥ ሠርተው ምግብ ቤት ለመክፈት ወሰኑ፡፡ መኖሪያቸው ካምፕ ውስጥ ስለነበር፣ እዚያ ያሰቡትን ነገር ማድረግ እንደማይችሉ ያውቃሉ። ስለዚህ ከዚያ ወጥተው ቤት ለመከራየት ወሰኑ፡፡ የሚያውቋቸው ሰዎችና ጐረቤቶቻቸው ውሳኔያቸውን አልደገፉትም። “እንዴት የሞቀ ቤትሽን ለቀሽ ትወጫለሽ? ልጆቹን ያለ መጠጊያ ልታስቀሪ ነው ወይ? ተይ! እነዚህን ሕፃናት ይዘሽ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳትወድቂ …” በማለት መከሯቸው፣ ገሰጿቸው፡፡ እሳቸው ግን በልባቸው “ቤቴንና አቅሜን የማውቀው እኔ ነኝ፤ ይህንን ቤት እኔ አልሠራሁት፤ ደግሞም ቤቴ ውስጥ የሚሸጥም ሆነ የምግደረደርበት ንብረት የለም” በማለት ምክርና ግሳፄውን ችላ አሉት፡፡ ከዚያም ከካምፑ ወጥተው፣ የቤት ኪራይ ረከሰ ወዳለበት አካባቢ ሄደው የ8 ብር የቀበሌ ቤት ተከራዩ፡፡ “እሷንም ተጫርቼና 4 ብር ጨምሬ ነው የተከራየሁት” ብለዋል ወ/ሮ አማረች ዘለቀ፡፡
ወ/ሮ አማረች ዘለቀ በሆሳዕና ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ ትምህርታቸውን እስከ 10ኛ ክፍል ተምረው ትዳር ሲመሠርቱ ወታደር ባላቸውን ተከትለው ሀዋሳ ከተማ መኖር ጀመሩ፡፡ የትዳር ጓደኛቸውን ሞት ቢነጥቃቸውም ወደ ትውልድ ቦታቸው አልተመለሱም፡፡ ኑሮአቸውን በሀዋሳ ከተማ አድርገው፣ ከብዙ ዓመታት ከፍተኛ ትግልና ጥረት በኋላ ሚሊዮን ብሮች በማንቀሳቀስ ዛሬ በከተማዋ የመጀመሪያ የሆነ ባለ 5 ኮከብ ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ባለቤት ሆነዋል፡፡ “ሰው ጠንክሮ ከሠራ የድካሙን ዋጋ አያጣም” ይላሉ ወ/ሮ አማረች፡፡ እኚህ ጠንካራና ታታሪ ሴት ለሀዋሳ ከተማ፣ ለደቡብ ክልልና ለመላው ሀገራችን ጥሩ ተምሳሌት ሆነዋል ይላል፤ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፡፡ እንዴት? የሀዋሳን ከተማ የውሃ ቧንቧ መስመር የዘረጋው ኢዘኢ የተባለ ድርጅት ካምፕ ወ/ሮ አማረች ከተከራዩት ቤት አጠገብ ነበር፡፡
ሻይ እና ቡና እያፈሉ፣ ሽሮ ወጥ እየሠሩ፣ እንጀራ እየጋገሩ፣ … ለሠራተኞቹ መሸጥ ጀመሩ፡፡ የሚሠሩት ምግብ፣ የሚጋግሩት አምባሻ ጥራት ያለውና የሚያጠግብ ስለነበር፣ የውሃ ቧንቧ ከሚዘረጉት ሠራተኞች በተጨማሪ ዝቀተኛ ገቢ የነበራቸው ሰዎችም ወሬውን እየሰሙ ገበያው ለመደላቸው፡፡ ይሄን ጊዜ የሚያስተናግዱበት ቤት ጠበባቸው። በረንዳው ላይ ቅርጮ (ሳጠራ) ሠሩ፡፡ ገበያው ከዕለት ወደ ዕለት እየደራ ሲሄድ ሳጠራውም ጠበበ፡፡ ይኼኔ ከበረንዳው ፊት ለፊት ቦታ ስለነበር፣ ጣራው የቆርቆሮ ክዳን ያለው፣ ጐንና ጐኑ ክፍት የሆነ አዳራሽ ቢጤ ሠርተው ማስተናገድ ቀጠሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ወንበር ማቅረብ የማይታሰብ - ከቅንጦትም በላይ ቅንጦት የሆነ መስተንግዶ ነበር፡፡ ተመጋቢው እየበረከተ፣ በርጩማውም እየጠፋ ሄደ፡፡ ይኼኔ ዙሪያውን ለመቀመጫ የሚሆን መደብ ሠሩ፡፡ በዚህ ዓይነት ሲሠሩ ቆይተው አንድ ሌሊት አሳዛኝ አደጋ ተፈጠረ፡፡ ሌሊቱን የጣለው ከባድ ዶፍ ዝናብ የአዳራሹን ጣሪያ ደረመሰው፤ መደቡንም አፍርሶ ወሰደው፤ በርካታ መነገጃ ንብረታቸውንም አበላሸ። ወ/ሮ አማረች እንደልማዳቸው ማልደው ሲነሱ፣ የነበረው እንዳልነበረ ሆኖ አገኙት፡፡ “ከእንግዲህስ መቋቋሚያዬን ይዣለሁ፤ ልጆቼንም የሰው እጅ ሳያዩ ጥሩ አድርጌ አሳድጋለሁ …” ያሉበት ንብረት በአንድ ሌሊት ከባድ ዝናም ወድሞ ብዙ አከሰራቸው፡፡ ወገባቸውን ይዘው በጣም አዘኑና “የራሱ ጉዳይ ነው በጠፋ ነገር ላይ ማዘን አያስፈልግም፤ ውሃ መውቀጥ ነው” ብለው ከሰው ገንዘብ ተበድረው ወደ ሥራቸው ተመለሱ፡፡ እየሠሩም ዕዳቸውን ከፈሉ፡፡ ከዚያም በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ኪሳራ ደርሶባቸዋል፡፡ ግን ተስፋ የቆረጡበት ጊዜ የለም፡፡ ከሰው እየተበደሩ፣ ሠርተው እየከፈሉ እዚህ መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ አማረች እዚህ ደረጃ የደረሱት በሕዝቡ ከፍተኛ ድጋፍ መሆኑን ደጋግመው ነው የሚናገሩት። ከባድ ዝናብ የሠሩትን አዳራሽ ጥርምስ ሲያደርግባቸውና የሠሩትን መደብ ባፈረሰባቸው ጊዜ ተመጋቢውን እፍ እፍ ብለው በርጩማም ሆነ ሌላ ነገር ላይ ሲያስቀምጧቸው ቅሬታ እንዳልነበራቸው ይናገራሉ፡፡ ለገቢያቸው መድራት ሌላው ምክንያት የደንበኞችን ባህርይ ማጥናት ነው፡፡ “ይህ ተመጋቢ ምን ያስፈልገዋል? እያልኩ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ ተመጋቢ ምን ያስደስተዋል? አዘውትሮ የሚፈልገው ምን ዓይነት ምግብ ነው? እገሌ’ኮ የሚወደው እንዲህ ነው፤ … እያልኩ በመሥራቴ የደንበኞቼ ቁጥር በየጊዜው ይጨምር ነበር፡፡ አሁንም አንዳንድ ሰዎች እየመጡ “ድሮ ልጆች ሳለን እዚህ ቦታ ሳጠራ ውስጥ ተመግበን ነበር” ይሉኛል፡፡ አንድ ጊዜ የተመገበ ሰው ዳግመኛ የሚመጣው እኔ ጥሩ ምግብ ስለምሠራ ነው፡፡ ሰውን አስደስቼ፣ ራሴም ቋሚ ጥሪት ማፍራቴ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ወደፊትም ዕድሜ እስከሰጠኝ ድረስ መሥራቴን እቀጥላለሁ” ብለዋል ወ/ሮ አማረች፡፡ “ውጤት ለማግኘት ጠንክሮ መሥራትና ተስፋ ያለመቁረጥ ያስፈልጋል፡፡ እኔ በብዙ ችግር ውስጥ ነው ያለፍኩት፡፡
ማንኛውም ሰው ችግር ሲያጋጥመው ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም ለመውጣት መጣር ነው እንጂ ዝም ብሎ መቀመጥ የለበትም፡፡ እኔ የመጀመሪያ ጥረቴ ልጆቼን ማሳደግ ነበር፡፡ መሥሪያዬን ሳላሟላ የቤት ዕቃ እንኳ አልገዛም ነበር፡፡ ዕቃውም፣ ንብረቱም፣ ቤቱም አብሮ ሲያድግ ነው ደስ የሚለው” ይላሉ፡፡ ሳጠራ ቤት ውስጥ ሲሠሩ ትንሹ ምግብ 0.60 ሳንቲም፣ ትልቁ 1.25፤ የሌሎችም ዋጋ በሳንቲም ቤት እንደነበር ወ/ሮ አማረች ያስታውሳሉ፡፡ አሁንም የሆቴላቸው ምግብ በጥራት በመሥራትና ብዙ በማቅረብ ታዋቂና ተመራጭ ቢሆንም፣ በዋጋ ረገድ ግን ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለች፤ ባለፈዉ ቅዳሜ ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር፣ በ1970 ዓ.ም ሆቴሉ የቅርጮ (ሳጠራ) በነበረበት ወቅት እዚያ መመገባቸውን ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ደግሞ በሆቴሉ ባይገለገሉም ወ/ሮ አማረች የሚጋግሩት አምባሻ ትልቅና የሚያጠግብ ስለነበር፣ የውሃ ባንቧ የሚዘረጉት ሠራተኞች “ወደ ሴንትራል እንሂድ” ይሉ እንደ ነበር መስማታቸውንና “ሴንትራል” የሚለው ስምም ከዚያ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡ “ልጆች እያለን ከት/ቤት ስንመጣ ምሳ ሳንበላ ሁላችንም መስተንግዶ ላይ እንሰማራ ነበር፡፡
ግማሾቻችን ዕቃ እናጥባለን፣ ምግብ እናቀርባለን፣ የተቀረነው ደግሞ ቤት የሚጋገረው እንጀራ ትንሽ ስለሆነ ሲያልቅ ሮጠን እንጀራ ገዝተን እናመጣ ነበር” ያለው የቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅና የሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍትህ ወ/ሰንበት ነው፡፡ ዝናብ ያፈረሰውን አዳራሽ እንዴት መልሰው እንደሠሩና የሴንትራል ሆቴልን ዕድገት እንዲህ ሲል አስረድቷል፡፡ ሚስማር የሚመታ አናጢ ይኖራል እንጂ ቤት ውስጥ ያለነው ሁላችንም ነበር የሠራነው። እዚያ እየሠራን የምሳ ሰዓት ሲደርስ ተሯሩጠን እናስተናግዳለን፡፡ የምሳ ሰዓት ሲያበቃ ደግሞ ወደ ሥራው ተመልሰን እየሠራን የአዳራሹ ሥራ አለቀ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ከዚያኛው አዳራሽ ፊትለፊት ቦታ ስለነበረ፣ ጣሪያ ያለው፣ ጀርባው ብሎኬትና ፊት ለፊቱ ክፍት የሆነ ሌላ አዳራሽ ሠራን፡፡ በሁለቱ አዳራሾች እየሠራን ብዙ ጊዜ ከቆየን በኋላ፣ ያለንበትን የቀበሌ ቤት በሊዝ ገዝተን፣ የመጀመሪያውን ሴንትራል ሆቴል ግንባታ ያለ ምንም የባንክ ብድር በድፍረት በነበረን ብር ቁፋሮ ጀመርን፡፡ መጀመሪያ የተሠራው የሕንፃው አዳራሽ ነበር። አንደኛው ፎቅ ሲሞላ ከስር ትልልቅ ሠርጐች ይካሄዱበት ነበር፡፡
ሥራው ለአንድም ቀን ሳይቆም ከላይ አርማታ እየተሞላ ከስር ሠርግ እየተደገሰ፣ በምሳ ገቢው ሲሚንቶ እየተገዛ፣ የእራቱ ደግሞ ለሠራተኛ እየተከፈለ የመጀመሪያው ሕንፃ ግንባታ ከሦስት ዓመት በፊት ሙሉ በሙሉ አለቀ” ብሏል አቶ ፍትህ፡፡ የመጀመሪያው ሕንፃ ግንባታ እንዳለቀ፣ ከጐናቸው ያለውን ቦታ ከግለሰብ ገዙ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የቀበሌ ቤት ስለነበር በሊዝ ገዝተው፣ ያላቸው የቦታ ስፋት 2400 ካሬ ሜትር ደረሰ፡፡ ከዚያም የዛሬ ሳምንት የተመረቀው ባለ 5 ኮከብ ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ግንባታ ያለ ምንም የባንክ ብድር መጀመሩን አቶ ፍትህ ተናግሯል፡፡ የዚህም የሥረኛው ወለል ተሠርቶ ሲያልቅ፣ ዙሪያውን ጨርቅ አልብሰው ሠርግ ያስተናግዱበት ነበር፡፡ የስሩን ጨምሮ ባለ 10 ፎቅ ሕንፃ አዳራሹ፣ ሠርግ ሳያስተናግድ የቀረበት ጊዜ እንደሌለ ሥራ አስኪያጁ ተናግሯል፡፡ የሕንፃውን ግንባታ በራሳቸው ገንዘብ ካጠናቀቁ በኋላ ለውስጥ ዕቃዎች ማሟያ ገንዘብ አጠራቸው። በዚህ ጊዜ መንግሥት ዘርፉን ለማበረታታት የፈቀደውን ከቀረጥ ነፃ መብት ለመጠቀም ወደ ዳሽን ባንክ አመሩ፡፡ “ከቀረጥ ነፃ መብት በመጠቀም በአንድ ጊዜ ብር ይዘን ውጭ አገር መሄድ ነበረብን፡፡ ያን ጊዜ ወደ ባንክ ሄድን፡፡ እኔ፣ ወንድሜና የግንባታ ተቆጣጣሪው ወደ ቻይና ሄደን ለሆቴላችን ጥራት ያለው ዕቃ ስንመርጥ ወር ቆየን፡፡ በዚያን ጊዜ ውስጥ የቻይናን ምግቦች መልመድ አልቻልንም።
ጧት ዳቦ በማርማላት ወይም በለስላሳ በልተን ዕቃዎቹን ወደምንመርጥበት ገጠር እንሄዳለን። እዚያ ደግሞ ምንም ምግብ የለም፡፡ ፆም ውለን ከምሽቱ 4 እና 5 ሰዓት እንመለሳለን፡፡ በዚህ ዓይነት የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑትን ዕቃዎች አዝዘን ተመለስን፡፡ ሁለተኛ ዙርም ሄደን ያዘዝናቸውን 43 ኮንቴይነሮች ዕቃ አመጣን፡፡” ብሏል፡፡ የዛሬ ሳምንት ሆቴሉ ተመርቆ እንዳበቃ ከሰዓት በኋላ፣ በተለያዩ አዳራሾች ሁለት ሠርጐች ሲስተናገዱ አይቻለሁ፡፡ አቶ ፍትህ በአንድ ቀን 14 ሠርጐች ያስተናገዱበት ጊዜ እንደነበር ተናግሯል። ሁለቱ መንትያ ሕንፃዎች በአጠቃላይ ትንሹ 40 ትልቁ ደግሞ 1000 ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉ ሰባት አዳራሾች አሏቸው፡፡ አዳራሾቹ በአካባቢው ስም ነው የተሰየሙት፡፡ የመጀመሪያውና ትልቁ አዳራሽ ልደት ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ይባላሉ፡፡ ሌላኛው የሲዳማ የፍቼ በዓል በሚከበርበት ስፍራ በጉዱማሌ ተሰይሟል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ግርጌ ባለው ታቦር ተራራም የተሰየመ አዳራሽ አለ፡፡ ሌላኛው ዘመናዊ አዳራሽ ደግሞ በቅርቡ በሞት በተለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም ተሰይሟል፡፡ “አዳራሾቹ እረፍት የላቸውም፡፡ ከሰኞ እስከ ዓርብ የተለያዩ ስብሰባዎች ያስተናግዳሉ፡፡ እሁድና ቅዳሜ ደግሞ ሠርግ” ብሏል አቶ ፍትህ፡፡ በከተማይቱ በርዝመቱ ቀዳሚ የሆነው ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል፤ ከ202 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ ሲሆን በሰባት ፎቆች 74 የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡
ከዚህ ውስጥ 23ቱ ሁለት አልጋ ያላቸው ክፍሎች ሲሆኑ በአጠቃላይ 97 እንግዶች ማስተናገድ ይችላሉ፡፡ ፕሬዚዴንሽል ስዊት፣ ስታንዳርድ፣ ደሉክስና ክላሲክ ይባላሉ፡፡ ሆቴሉ በሁለተኛ ፎቁ የመዋኛ ገንዳ በመያዝ ከከተማዋ ቀዳሚው መሆኑን አቶ ፍትህ ገልጿል። በሕንፃው የመጨረሻ ፎቅ (ቴራስ) በስተደቡብ ታቦር ተራራን፣ በስተደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሐዋሳን ሐይቅ፣ በስተምስራቅ ደግሞ በፕላን የተሠራችውን የሀዋሳ ከተማን እየቃኙ ይዝናናሉ፡፡ በተለያዩ መጫወቻዎች የተደራጀ የሕፃናት መዝናኛም ይዟል፡፡ “እንግዶች ልጆቻቸዉን ይዘው ወደተለያዩ ሆቴሎች ሲሄዱ የልጆቻቸዉን ደህንነት ለመጠበቅ ዘና ብለው አይዝናኑም፡፡ እኛ ጋ ግን እንደ “ዴይኬር” የሠለጠኑ ባለሙያዎች ልጆቹን ተቀብለው ያዝናናሉ፤ ይጠብቃሉ፡፡
ስለዚህ ወላጆችም ልጆችም ያለ ስጋት በምቾት ይስተናገዳሉ” ብሏል፡፡ የሴቶችና የወንዶች ፀጉር ቤት፣ ሁለቱም ፆታዎች በተለያየ ክፍል የሚገለገሉበት ስፓና ሳውና ባዝ፣ የተደራጀ ጂምናዚየምና መታሻ (ማሳጅ)፣ የተለያየ መጠን ያላቸው ባርና ሬስቶራንቶች፣ ለሆቴሉ ሠራተኞችና ለእንግዶች የመጀመሪያ ዕርዳታ የሚሰጥ ክሊኒክ አለው፡፡ መናኸሪያ አካባቢ 18 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ፔንሲዮንም አላቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ባለ 17 ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ ለመገንባት የአፈር ምርመራና ፕላን ማሻሻያ እያሠሩ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግሯል። ወ/ሮ አማረች ሐይቁ አካባቢ ለአንደኛው ልጃቸው ዘመናዊ ጋራዥ የከፈቱለት ሲሆን በጋራዡና በሐይቁ መካከል ደግሞ ለማንም ያልተሰጠ ቦታ አለ፡፡ ያንን ቦታ ማዘጋጃ ቤቱ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የሐይቁ መዳረሻ የሆነው ይህ ቦታ ከተፈቀደላቸው የተለያዩ የዱር እንስሳት የያዘ “ዙ” እና “ሪዞርት” ለመሥራት አቅደዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሆቴልና ለግል አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖች፣ ለሠርግ የሚከራዩ ማርቸዲሶች አላቸው፡፡ አስጐብኚ ድርጅትም ለመክፈት ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ አቶ ፍትህ ገልጿል፡፡
እንግዶቻቸውን ከቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ተቀብለው በመንገዳቸው ያሉትን የመስህብ ስፍራዎችና መዝናኛዎች (ለምሳሌ ላንጋኖ፣ …) እያስጐበኙ ሀዋሳ ለማድረስ አቅደዋል፡፡ የሆቴሉ የስር ወለል (ግራውንድ ፍሎር) ሁለት አገልግሎት ይሰጣል፣ ናይት ክለብና ለቪ አይፒ መኪኖች ማቆሚያ፡፡ ዘመናዊው ናይት ክለብ ማታ እስከ 4 ሰዓት ባህላዊ ዝግጅቶች፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ዘመናዊ ጭፈራ ያስተናግዳል፡፡ ወ/ሮ አማረች በችግር ያሳደጓቸውን ልጆች ለወግ ለማዕረግ አብቅተው የልጅ ልጅ አይተዋል፡፡ አሜሪካ የሚኖረው አቶ ሙሉቀን ትዳር መስርቶ ሁለት ልጆች ወልዷል፡፡ አቶ ፀጋዬም አራት ልጆች አፍርቷል፡፡ አቶ ፍትህና አቶ ታገል ደግሞ በቅርቡ እንደሚሞሸሩ ወ/ሮ አማረች ዘለቀ ተናግረዋል፡፡ ስለ ሆቴሉ ዋጋም አቶ ፍትህ ሲናገር “ዋጋችንን የከተማው ነዋሪ የሚመሰክረው ነው፡፡ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ኪስ ያገናዘበ ነው፡፡ ውድ ዋጋ ለማስከፈል ያሉን ፋሲሊቲዎች ከበቂ በላይ ናቸው። ነገር ግን እናታችን ሁሉም ተደስቶ፣ የሁሉም ቤት ሆኖና ተስተናግዶ የምናገኘው ነው የሚሻለው የሚል መመሪያ ስላላት፣ ዋጋችን የኅብረተሰቡን ኪስ የሚጐዳ አይደለም፡፡ ከዋጋችን ዝቅተኛነት የተነሳ ከአዲስ አበባ መጥተው ሠርግ የሚያስደግሱ አሉ፡፡ በሀዋሳና በዙሪያዋ የሚገኙ ሰዎች እዚህ ነው የሚደግሱት፡፡
ጠዋት ተነግሮን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሁለት ሺህ ሰው ምሳ ማዘጋጀት እንችላለን፡፡ እኛ እንደ እናት ሆነን ነው የምንደግሰው፡፡ ሌላው ጋ የሚበላው ነገር ሲያልቅ “ማለቅ ራሱ ዓይነት ነው” ይባላል፡፡ እኛ ጋ ግን እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም። የመጨረሻው ሰው ክትፎም ሆነ ቁርጥ ተስተናግዶ ነው የሚሄደው፡፡ በምግብ ጥራት፣ በብዛትና በዋጋ ተወዳዳሪ የለንም፡፡ “ትልቁ አልጋችን ፕሬዚዴንሻል ሱዊት ነው። ሦስት መኝታ ክፍሎች፣ ጃኩዚና ስቲም ባዝ፣ የራሱ ኪችንና አነስተኛ መሰብሰቢያ፣ አውቶማቲክ የሽንት ቤት መቀመጫ፣ … ኖሮት አራት ሺህ ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ ሌላ ቦታ ተመሳሳይ ክፍል ያላቸውና ከእኛም ወረድ የሚሉት ከ8 እስከ 9ሺ ብር ይከራያሉ፡፡ ሱት የሚባለውና ሳሎን ያለው ክፍል፣ ሌሎች 120 ዶላር ነው የሚያስከፍሉት፡፡ እኛ ጋ ግን 1500 ብር ነው፡፡ ዴሉክስ፣ ክላሲክና ቱዊንስ የሚባሉት፣ እኛ ዘንድ 800 ብር ነው የሚከራዩት፡፡ ሌላው ጋ ግን በዶላር ሂሳብ ሆነው 1200 ብር ገደማ ናቸው፡፡ ማንም ሰው ደፍሮ ሊተኛበት የሚችለው ስታንዳርድ የሚባለውን ክፍል 400 ብር ነው የምናከራየው፡፡
እዚህ ባለ 5 ኮከብ አገልግሎት እያገኙ በ400 ብር ማደር ይቻላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዋጋችን አካባቢ ተኮርና የደንበኞቻችንን ኪስ የማይጐዳ ስለሆነ ውድ አይደለም ማለት ነው” ሲል አስረድቷል፡፡ ሁሉም ክፍሎች (መፀዳጃ ክፍል ጭምር) እንግዳው ችግር ቢያጋጥመው ጥሪ የሚያደርግበት ስልክ አላቸው። ሕንፃው ሽቦ አልባ መገናኛ (ዋየርለስ) ስላለው፣ ማንኛውም ሰው ኢንተርኔት በነፃ መጠቀም ይችላል። ክፍሎቹ በሙሉ ሲጋራ አይጨስባቸውም። ማጨስ ለሚፈልግ ሰው ግን ኮሪደር ላይ ማጨሻ ስፍራ ተዘጋጅቶለታል፡፡ በሁሉም ፎቆች ኮሪደሮች የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራና እሳት ማጥፊያ ተገጥሟል፡፡ ክፍሎቹ ደግሞ ቲቪ፣ ስልክ፣ ካዝና፣ ፍሪጅ፣ እንደ ክፍሎቹ ደረጃ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ መደበኛ ሻወር፣ ፀጉር ማድረቂያና፣ ሳሎን፣ መዝናኛ ሶፋና ጠረጴዛ፣ የጽሕፈት ጠረጴዛና ወንበር፣ ሻይና ቡና ማፊያ፣ በረንዳ፣ … አላቸው፡፡ እንዲሁም ሆቴሉ ሁለት አሳንሰር (ሊፍት) አሉት፡፡ ሆቴሉ ለ252 ዜጐች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን የሠራተኞቹን ቁጥር 300 ለማድረስ ዕቅድ አለው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር