ድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያን ያለአግባብ የመጠቀም ልማድ መስፋፋቱ አሳሳቢ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ድንገተኛ የወሊድ መቆጣጠሪያ /ፖስት ፒል/ን ያለአግባብ የመጠቀም ልምድ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን የጤና ባለሙያዎች ይገልፃሉ ፡፡
ይህ መድሃኒት አንዲት ሴት ተገዳ ወይም ሳታስብ በፈጸመችው ወሲብ ላልተፈለገ እርግዝና እንዳትዳረግ ለመከላከል የሚመረት የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው ።
አንዳንድ የመድሃኒት መደብር ባለቤቶች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ግን ፥ መድሃኒቱን በተደጋጋሚ እየገዙ የሚጠቀሙ ሴቶች አጋጥሟቸዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ መድሃኒቱን ቋሚ የወሊድ መቆጣጠሪያ አደርገው የመጠቀሙ ልማድ እየተስፋፋ መጥቷል ይላሉ ።
ያነጋገርናቸው የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ፥ ሰዎች በዚህ መድሃኒት ተማምነው የሚፈጽሙት ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ከሚታሰበው የእርግዝና ስጋት በበለጠ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ጨምሮ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች እየዳረጋቸው ነው።
በተለይም ባለትዳሮች ፣ ወጣቶችና ከአንድ በላይ የፍቅር ጓደኛ ያላቸው ሁሉ አማራጫቸውን ሌሎች የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን እንዲያደርጉ ነው የሚመክሩት ።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በከተማ ጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ረዳት ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ አበባ እንደሚሉት ፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መድሀኒቱን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ሲያደርግ ዓላማው አሁን ሰዎች ከሚተገብሩት ልምድ ጋር ፈጽሞ የተራራቀ እንደሆነ ይናገራሉ።
ተገዳ የተደፈረች ሴትና የእርግዝና መከላከያ ባልተወሰደበት ሁኔታ ለተፈጸመ የግብረስጋ ግንኙነት እርግዝናን ለመከላከል እንዲቻል የሚያስችል መፍትሄ ሆኖ ሳለ በተለይ ወጣቶች አማራጮች ባልጠፉበት ሁኔታ እንደ አንድ ወሊድ መቋጣጠሪያ አድርገው መውሰዳቸው አግባብ እንዳልሆነም ነው የተናገሩት ።
ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ እንዲቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በሰፊው ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰፊ እቅድ እንደያዘም ገልፀዋል ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር