“ከምርጫው በኋላም እስሩና እንግልቱ ቀጥሏል” የሲዳማ አርነት ንቅናቄ


ባለፈው ሳምንት ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረው እጩዎቼ፣ ታዛቢዎቼና አባላቶቼ በእስር፣ በድብደባና ከሥራ በመባረር እየተንገላቱ ነው በማለት ራሱን ከምርጫው ያገለለው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፤ ከምርጫው በኋላም እስሩና እንግልቱ መቀጠሉን አስታወቀ - በአንድ ሳምንት 26 አባላቱ እስር እንደተፈረደባቸው በመግለፅ፡፡ በሲዳማ ዞን በየወረዳው ጊዜያዊ ፍርድ ቤቶችና ሸንጎዎች እየተቋቋሙ የፓርቲው እጩዎች፣ ታዛቢዎችና አባላት ከ400 ብር በላይ የገንዘብ ቅጣትና ከ3ወር እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚደርስ እስራት እየተፈረደባቸው ወህኒ መውረዳቸውን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የደርጅቱ ጉዳይ ሃላፊ ዶ/ር አየለ አሊቶ ገልፀዋል፡፡
ከምርጫ ሂደቱ ጀምሮ ከምርጫ በኋላም እንግልቱ ቀጥላል ያሉት ዶ/ር አየለ አሊቶ፤ የኢህአዴግ አመራሮች ከሳሽም ፈራጅም በሆኑበት ሁኔታ ዜጎቻችን እየተንገላቱ ነው፤ ከምርጫው ብንወጣም ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ፓርቲው በአዲስ አበባና አካባቢ ምርጫ ላለመሳተፍ ከወሰኑት 33 ፓርቲዎች በመነጠል “በሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ነው” በሚል በምርጫው ለመወዳደር የምርጫ ምልክት ከወሰደ በኋላ ነው ራሱን ከምርጫው ያገለለው - እጩዎቼና ታዛቢዎቼ ላይ እንግልት ደረሰ በሚል፡፡ የምርጫ ቦርድ በበኩሉ ጉዳዩን ማጣራቱን ጠቁሞ የፓርቲው ክስ መሠረተ ቢስ መሆኑን ደርሼበታለሁ ሲል ለኢቲቪ ገልጿል - ባለፈው ሳምንት፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር