አዲሱ የኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው


አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው የቋንቋ ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው።
ረቂቅ ፖሊሲው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሀገራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ጋር በመተባበር በባለድርሻ አካላት ሲገመገም ነው የቆየው።
ትላንትና ከትናንት ወዲያ  በተካሄደው የመጨረሻ ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ፥ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ 230 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
በሚኒስቴሩ የቋንቋና የባህል ልማት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ሹምነካ እንዳሉት ፖሊሲው የግልና የጋራ የቋንቋ መብቶችን የያዘ ነው።
ከፊደል ቀረጻ ጀምሮ እስከ ትግበራ ያለው ሂደት በስርዓት እንዲመራ ፖሊሲው አጋዥ ይሆናል ሲሉ አቶ አውላቸው ለሪፖርተራችን ራሔል አበበ ነግረዋታል።
በመድረኩ የቋንቋና የህግ ማዕቀፍ፣ ቋንቋና አፍ መፍቻ ፣ ቋንቋና ከፍተኛ ትምህርት የሚሉና ሌሎችም 10 ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ፥ በቋንቋ ዙሪያ የህንድና የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የቋንቋ መብቶች በተገቢው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑና እንዲደረጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል የተባለው ፖሊሲ ግብአት ከተሰበሰበት በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር