ፌዴሬሽኑ ከደቡብ እግር ኳስ አመራር ጋር የደረሰበት ስምምነት አለመግባባት ፈጠረ


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ከቆየ በኋላ፣ ባለፈው ሚያዝያ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ሁለቱ ፌዴሬሽኖች ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ ከስምምነት ቢደርሱም፣ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚዎች ውስጥ አለመግባባት መፍጠሩ ተሰማ፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ በፌዴሬሽኑ ልዩ ልዩ ክፍሎች ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ሙያተኞችና ሠራተኞች ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ስብሰባ፣ በፌዴሬሽኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደተነጋገሩ፣ የፌዴሬሽን ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደምንጮቹ፣ በዕለቱ በተካሄደው ስብሰባ በፌዴሬሽኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ነጥቦች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ ነጥቦች ላይ የጋራ መግባባት ሲፈጠር፣ በአንዳንዶቹ ግን በተለይም ሥራ አስፈጻሚዎቹን ለሁለት በመክፈል ክፉና ደግ አነጋግሯል፡፡

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መካከል አለመግባባት ከፈጠሩት ነጥቦች፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ያለ ሥራ አስፈጻሚው ይሁንታ ወደ ሐዋሳ በማምራት ከደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ልዩነቱን ለማጥበብ የደረሱበት ስምምነት እንደሆነ ምንጮቹ ያስረዳሉ፡፡ 

በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ተደረሰበት የተባለው ስምምነት ‹‹የደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መጋቢት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በሐዋሳ ጠርቶት የነበረው ስብሰባ ከመነሻው ሁለት ተልዕኮዎች እንደነበሩት፣ አንዱና የመጀመርያው በክልሉ ያለውን የስፖርት ልማት እንቅስቃሴ ለተጋባዥ የክልል ፌዴሬሽኖችና ከተማ አስተዳደሮች በማስጐብኘት ልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ በሌላው ደግሞ የከተማና የክልል ፌዴሬሽኖችን አደረጃጀትና አወቃቀርን በተመለከተ ክልሉ ጥናት አስጠንቶ ለውይይት ማቅረብ›› በሚሉት ሁለት ነጥቦች ተገቢነት ላይ ውይይት አድርገው በሁለቱም በኩል ጥፋት ያሉትን እንዳስቀመጡ መግለጫው ያስረዳል፡፡ 

ጥፋት የተባለው ደግሞ፣ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በራሱ ጊዜ በጠራው ስብሰባ ላይ ሊቀርብ የነበረው የፌዴሬሽኖች አደረጃጀትና አወቃቀር ላይ ሊቀርብ የነበረው ጥናታዊ ጽሑፍ ጉዳዩ አገራዊ ሆኖ ሳለ፣ ይህም መመራት የሚገባው በሚመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካይነት መሆን ሲገባው፣ የክልሉ ፌዴሬሽን ከተሰጠው ተልዕኮና ሥልጣን ውጭ መንቀሳቀሱ ተጠቅሷል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ደግሞ፣ የተዘጋጁት አጀንዳዎች በአንድ በኩል የልምድ ልውውጥ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ የተመሠረተው ውይይት ተገቢነት፣ በሌላ በኩል የክልል ፌዴሬሽኖች አደረጃጀትና አወቃቀር ላይ ያለው አጀንዳ በጥቅሉ አይቶ በልምድ ልውውጡ ላይ መወያየት እንዲችሉ፣ ነገር ግን በፌዴሬሽኖች አደረጃጀትና አወቃቀር ላይ ግን ከመተዳደሪያ ደንቦችና መመሪያዎች አኳያ ተገቢ አለመሆኑን ለይቶ በመግለጽ ውይይት እንዲደረግበት ማድረግ ሲቻል፣ በጥቅሉ ስብሰባው እንዲቋረጥ ትዕዛዝ መስጠቱ ስህተት ተብሎ ተወስዷል፡፡ ወጪን በተመለከተ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አጣርቶ እንዲተካ የሚልም በመግለጫው ተካቷል፡፡

ይሁንና የስምምነቱን ዓይነትና ምንነት አስመልክቶ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ለሥራ አስፈጻሚውና በዕለቱ በስብሰባው ለተካፈሉ አካላት ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ ግን ‹‹ስምምነቱ›› በሥራ አስፈጻሚዎቹ መካከል አለመግባባት ሊፈጠር እንደቻለ ነው ምንጮች ያስረዱት፡፡ በዚሁ መሠረት የመጀመርያውን ቅሬታ ያቀረቡት ወ/ሮ ጥሩወርቅ ብርሃኑ እንደሆኑና እሳቸውም፣ ከደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ከመከሰቱ በፊት የነበረውን ሒደት እንደ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ማወቅ ሲገባቸው ያልተደረገበት ምክንያት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል ይላሉ፡፡ 

እንደምንጮቹ ከወ/ሮ ጥሩወርቅ ብርሃኑ ቀጥሎ የአቶ ሳህሉን ሪፖርት በመቃወም አስተያየት የሰጡትና ከአፋር ክልል የተወከሉት አቶ አሊሚራህ መሐመድ ናቸው፡፡ እሳቸውም በዚህ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሆነው እንቅስቃሴ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹በርካታ ውሳኔዎች በኢመርጀንሲ ስም በሚተላለፉ ውሳኔዎች ደስተኛ አይደለሁም፤›› ብለው የገለጹበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ‹‹ከደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት የሆነው ስብሰባ የተፈቀደው በማን በኩል ነው? የተከለከለበትስ ምክንያት ምንድን ነው? በሪፖርቱ እንደተነገረው፣ ውሳኔውን ያስተላለፈው ኢመርጀንሲ ኮሚቴ ከሆነስ እርስዎ ልዩነት ያሉትን ችግር ለማጥበብ ወደ ሐዋሳ ሄደው የተደራደሩት ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ከማንኛችን ጋር ተነጋግረው ነው? ኢመርጀንሲ የሚባለው አካሄድስ እስከ መቼ ነው? በኢመርጀንሲ ኮሚቴ ብቻ የፌዴሬሽኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚከወን ከሆነ እኔን ጨምሮ የብዙዎቻችን ውክልና ትርጉሙ ምንድን ነው?›› የሚል ጠንካራ መከራከሪያ አንስተው ቤቱን ለሁለት ከፍለውት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ 

ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ነጥብ፣ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን መጋቢት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ሊያከናውነው ለነበረው ስብሰባ ያወጣውን ወጪ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኪሳራውን አጣርቶ ይተካል የሚለው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም በአመራሩ ውስጥ የሐሳብ ልዩነት መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰረ የተባለው የገንዘብ መጠንም 69 ሺሕ ብር መሆኑን ጭምር ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር