ለኢቴቪ ዓመቱን ሙሉ “April the fool” ነው!

ሰሞኑን የተከሰተ ዜና ነው - እዚህ ሳይሆን ፈረንጆቹ አገር፡፡ ሁለት ታዳጊ ፍቅረኛሞች ናቸው አሉ፡፡ የፍቅር ጓደኝነት ከመሰረቱ ብዙ አልቆዩም፡፡ ግን ሲዋደዱ ለጉድ ነው፡፡ (እንደ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች እንዳትሉኝ!) ባለፈው ሰኞ ግን በጨዋታ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት እሷ እሱን አንገቱ ላይ በስለት ወግታው ወህኒ ወረደች አሉ (የአፍሪካ ፖለቲካ አይመስልም?) አያችሁ እንዲህ በጨዋታ መሃል ያልተጠበቀ አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡ አንዳንዴ ዓይን ሊጠፋ ወይም እግር ሊሰበር ይችላል፡፡ ባስ ሲል ህይወትም ይጠፋል፡፡ በፍቅር ጨዋታ እንዲህ ካጋጠመ በፖለቲካ ጨዋታ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል አስቡት፡፡
እቺን እቺንማ ከእኛ በላይ ማን ያውቃታል? ምንም ቢሆን እኮ የአፍሪካ ልጆች ነን! (የአራዳ ልጅ እንዲሉ) የጨዋታው አባቶች የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ከሆኑ ደግሞ ነገርዬው የከፋ ይሆናል - የመረረ!! ለምን መሰላችሁ? መቼ እንደሚያመሩ፤ መቼ ከፍቅር ወደ ጥላቻ እንደሚሸጋገሩ ፈጽሞ አታውቁም፡፡ ኳስ ይዞ የነበረው እጃቸው በምን ቅጽበት ጠብመንጃውን አፈፍ እንዳደረገ ፈጣሪያቸው ብቻ ነው (የራሳቸው ፈጣሪ ይኖራቸዋል ብዬ እኮ ነው!) የሚያውቀው (“አድነነ ከመዓቱ” ማለት ይሄኔ ነው!) ይኸውላችሁ የእኔ ነገር የፍቅረኞቹን ሳልጨርስላችሁ ፖለቲካ ውስጥ መሰስ ብዬ ገባሁላችሁ፡፡ (ፖለቲካ አሳሳች እኮ ነው!) እናላችሁ.. ሁለቱ ፍቅረኛሞች ሲገናኙ ሁሉም ነገር አማን ነበር፡፡ በተለይ እሱ ፍቅር እንጂ ሌላ አልጠበቀም፡፡
እሷም ብትሆን ያለወትሮዋ ቀልድና ጨዋታ አምሯታል እንጂ ሌላ ነገር አላሰበችም፡፡ በጨዋታቸው መሃል ግን አንድ ዱብዕዳ ዜና ጣል አደረገችበት - እንደዘበት! “አርግዣለሁ” አለችው፡፡ “What?” (ምን? ትቀልጃለሽ? አብደሻል? ወዘተ… ሊል እንደሚችል ገምቱ!) ፍቅረኛ ሆዬ ተወራጨ፣ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ! ነገሩ ወደ ክርክር …ጭቅጭቅ…ውዝግብ…ጠብ…አምባጓሮ…ተለወጠ፡፡ (በአጭሩ የአፍሪካን ፖለቲካ ሆነላችሁ!) ፍቅረኛዋ ራሱ የሰጣትን ሰንጢ አወጣችና ታስፈራራው ጀመር፡፡ ይሄኔ ፖሊስ ጋ እደውላለሁ አላት - ቢቸግረው፡፡ አሁን ባሰባት፡፡ ተንደርድራ እንካ ቅመስ አለችው፤ አንገቱ ላይ ሰካችበት፡፡ የአፍሪካ ገዢ ፓርቲዎች ተጫውተው ተጫውተው ሲያፍሩ ተቃዋሚዎቻቸውን እንደሚያደርጉት፡፡ እሱ ወደ ሆስፒታል፤ እሷ ወደ ወህኒ ቤት! ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ምን አለች መሰላችሁ? “ነገሩ ሁሉ ቀልድና ጨዋታ ነበር…ፖሊስ እጠራለሁ ሲል ነው ወደ ጠብ የተለወጠው” የአፍሪካ ገዢ ፓርቲዎች ቢሆኑ ደሞ እንዲህ ይሉ ነበር - በምርጫ ሳቢያ በተፈጠረ ሁከት ሰው ከገደሉና ተቃዋሚዎቹን ወህኒ ቤት ካጐሩ በኋላ “ሃሳባችን ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ነበር፤ ተቃዋሚዎች ግን ህገመንግስቱን በሃይል…ነገሩ ሁሉ ተበላሸ” አይገርማችሁም…አርግዣለሁ ያለችሁም እኮ ውሸቷን ነበር፡፡ እሷ ውሸታም ሆና ግን አይደለም፡፡ ቀኑ ነው፡፡ አዎ ቀኑ “አፕሪል ዘ ፉል” ነበር - ባለፈው ሰኞ አፕሪል 1 ቀን 2013 ዓ.ም፡፡ እናም ልጅት ልታቄለው ወይም ልታጃጅለው ብላ “አርግዣለሁ” አለችው፡፡
የበርዝዴይ ድንገተኛ ስጦታ (Surprise gift) ዓይነት እኮ ነው፡፡ ክፋቱ ግን ወዳልታሰበ ችግር (አደጋ ማለት ይሻላል) አመራ፡፡ በነገራችሁ ላይ ይሄን እለት (April Fools’ Day) አስመልክቶ በኢንተርኔት የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ “ሁሉም ሰው ለመጃጃል የተስማማበት ቀን!”፣ “ቀልድ የማይችሉ ሰዎች ቀልድ የሚሞክሩበት ቀን!”፣ “365 ቀናት ቀልደው ያልተሳካላቸው ሰዎች ዕድላቸውን የሚሞክሩበት ዕለት” በሚል ተገልጿል፡፡ ፈረንጆቹ ጋ ይሄ ቀን የሚከበረው በዓመት አንዴ ነው፡፡ እዚህ አፍሪካ ግን በየቀኑ፤ 366 ቀናት “አፕሪል ዘ ፉል” ነው! እኔን ካላመናችሁኝ የአፍሪካ ፖለቲከኞችን ጠይቋቸው - በዓል የለ…የሥራ ቀን የለ… ሰንበት የለ…በቃ ሁሌ ማጃጃል ነው - ማቂያቂያል! መሸወድ! ማሞኘት! ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚውን፤ ተቃዋሚው ገዢ ፓርቲውን፤ እንደገና ደግሞ እርስ በእርሳቸው - አፕሪል ዘ ፉል ሲባባሉ ይከርሙላችኋል፡፡ የማታ ማታም እንደ ፍቅረኛሞቹ ጨዋታው ወደ ፍጥጫ፣ ፍቅሩ ወደ ጠብ ይለወጣል፡፡ አንዱ ሌላውን በማጃጃል ቢያበቃማ እንዴት በታደልን ነበር (ዕዳው ገብስ ነዋ!) የዛሬ 51 ዓመት (እ.ኤ.አ በ1962 ዓ.ም) የስዊድን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ያደረገውን ልንገራችሁ፡፡
ያኔ በአገሪቱ ባለቀለም ቴሌቪዥን አልተጀመረም፡፡ አንድ የቲቪ ቻናል ብቻ ነበር ያለው (እንደኛ አንድ ለእናቱ!) የቲቪው አስተዋዋቂ በስክሪኑ ብቅ አለና ሰበር ዜና የሚመስል ነገር ተናገረ “አሁን የቴክኒክ ኤክስፐርታችን በቲቪያችሁ እንዴት ባለቀለም (ከለር) ምስል እንደምትመለከቱ ይነግራችኋል” ወዲያው ኤክስፐርቱ ቀርቦ ማብራራት ጀመረ፤ “ነገሩ ቀላል ነው…ስቶኪንግ ትፈልጉና ለሁለት በመቅደድ ስክሪኑን ትሸፍኑበታላችሁ፤ ይሄኔ ምስሉን ባለቀለም ያደርግላችኋል” ስውዲናዊው ሁሉ ስቶኪንግ ፍለጋ በየአልጋ ስሩ ያጐነብስ ገባ፡፡ ከሚስቱ ጋር የተጣላ ሁሉ ሳይኖር አይቀርም፡፡ “በቅርቡ የገዛሁልሽን ስቶኪንግ የት አገባሽው?” በሚል፡፡ አብዛኛው የስውዲን የቲቪ ተመልካች መሸወዱን የነቃው በኋላ ነው፡፡ ለካስ አፕሪል ዘ ፉል ነው! በነገራችሁ ላይ በስዊድን ባለቀለም ቴሌቪዥን የተጀመረው ከስምንት ዓመት በኋላ ነበር - እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም፡፡ ይኸውላችሁ የስዊድኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተመልካቹን “አፕሪል ዘ ፉል” ያለው በ50 ዓመት ታሪክ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ኢቴቪ እኮ በየቀኑ ነው “አፕሪል ዘ ፉል” የሚለን - 365 ¼ኛ ቀናት ያሞኘናል (ሩቧን እንኳ አይምረንም!) ምናልባት ግር ሊላችሁ ይችላል፡፡ አይፈረድባችሁም፡፡
ዓመቱን ሙሉ ሰውን ለማሞኘት እኮ “ጂኒየስ” መሆን ይጠይቃል፡፡ ኢቴቪ “ጂኒየስ” ነው ማለት ነው!! እስቲ ወደ ኋላ ሄዳችሁ በኢቴቪ የተላለፉ የሚተላለፉ ዜናዎችና ዘገባዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችን አስታውሱ፡፡ በአብዛኛው ማርና ወተት የሚፈስባት ኢትዮጵያን አይደል የሚስልልን፣ ኢኮኖሚዋ ያደገ የተመነደገ፣ ጥጋብ በጥጋብ የሆነች አገር እንዳለን ይሰብከን የለ! (የእኛን አገር ግን እኛ እናውቃታለን!) አርሶ አደሮች ሚሊዬነር እንደሆኑና በሃብት እንደተንበሸበሹ ደጋግሞ ሲነግረን አልሰማችሁም? የግብርና ምርት ማደጉንስ አልነገረንም? (ያውም እስኪሰለቸን!) እኛማ የዋሆቹ አምነን ተቀብለነው ነበር፡፡
ግን ዕድሜ ለኢህአዴግ! በ9ኛው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የኢቴቪ መረጃ የተሳሳተ መሆኑን በይፋ አረጋገጠልን፡፡ ተሳስቶ ግን አልነበረም፡፡ “April the fool” ማለቱ ነው! የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ራሱ የአርሶአደሩን ችግር ወረድ ብለን ልናይ ይገባል ያለው ወዶ እንዳይመስላችሁ - ከኢቴቪ“April the fool” ለመውጣት እኮ ነው! ኢቴቪ ነፍሴ…የውጭ አገር ጐብኝዎች ስለኢትዮጵያ በጐ በጐ ነገር ሲናገሩ ደጋግሞ በስክሪኑ ያሳየናል፡፡ የተናገሩትን በአማላይ ቃላት አስውቦ ይዘግብልናል፡፡ (አገራችንን የማናውቃት እየመሰለው!) ለምሳሌ አንድ ምሁር “የፌደራሊዝም ስርዓታችሁ በዓለም አንደኛ ነው” ብለው ያደንቁን ጊዜ አስራ ምናምን ጊዜ ተደጋግሞ ይቀርብልናል፡፡
ግን ደግሞ ኢትዮጵያን ደጋግመው የጐበኙ ፈረንጆች ስለሆቴሎቻችን መስተንግዶና የጥራት ደረጃ ዝቅተኛነት ኮስተር ብለው ሲናገሩ ከአንድ ጊዜ በላይ አያቀርበውም፡፡ አሃ! ኢቴቪ ዋና ሙያው መሸወድ ነዋ (አፕሪል ዘ ፉል!) እንደው መንግስት ምን ይለኛል ብሎ ነው እንጂ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የገባችው ኢህአዴግ እግሩ አዲስ አበባን ሲረግጥ ነው የሚል ዶክመንተሪ ፊልም ሰርቶ ቢያቀርብ ደስታውን አይችለውም፡፡ (የኢቴቪ ዶክመንተሪ ፊልሞች ትዝ አሏችሁ?) ኢህአዴግና መንግስት ግን እንቅፋት ሆኑበት፡፡ መካከለኛ ገቢ አገራት የምንገባው ዛሬ ሳይሆን በ20 እና 30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ብለው፡፡ (ይሄም አፕሪል ዘ ፉል እንዳይሆን?) ኢቴቪ አንዳንዴ የፈጠራ አቅሙ ሲዳከምበት ምን እንደሚያደርግ ታውቃላችሁ? ለ“April the fool” የሚሆን መግለጫ ወይም መረጃ ያላቸው የሚመስሉ የመንግስት ተቋማትን እየዞረ ያፈላልግና በኢንተርቪው ወይም በውይይት አሊያም በዜና መልክ ያቀርብልናል፡፡ (ያሞኘናል በሉት!) ለምሳሌ የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን የሃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት እየተጋ መሆኑን፣ ቴሌኮም የኔትዎርክ መጨናነቅን በአጭር ጊዜ እንደሚያቃልል፣ ውሃና ፍሳሽ ለህዝቡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ እየጣረ መሆኑን… በቅርቡ አልሰማንም? ኢቴቪ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ፡፡
ትንሽ ቆይቶ ግን የተባለው ሁሉ “April the fool” መሆኑ ገባን፡፡ ቆይ መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማጥፋትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ኢቴቪ የነገረን ስንቴ ነው? ያውም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን እየጋበዘ፡፡ ወዳጆቼ፤ ባለስልጣናትን ስላቀረበ ብቻ ነገሩ እውነት ከመሰላችሁ በጣም ተሸውዳችኋል! ነገርዬው “April the fool” ነው! ኢህአዴግ በ9ኛው ጉባኤ ላይ ምን አለ? የአመራሩ ችግር ኪራይ ሰብሳቢነትና አድርባይነት መሆኑን አልገለፀም? ኢቴቪ ግን የዚህን ተቃራኒ ሲሰብከን ነው የከረመው፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ በጉባኤው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ ሳይሆን ለመንግስት ብቻ እየሰሩ ነው፤ ደካማ ጐኑን እየተው ጠንካራውን ብቻ ያስተጋባሉ ሲል ተችቷል፡፡ ኢህአዴግና መንግስት እንደ ኢቴቪ አያብዙት እንጂ እነሱም እኮ የራሳቸው ብዙ “April the fool” አላቸው፡፡ ተቃዋሚዎችም ግን አንዳንዴ ያውቁበታል እኮ አፕሪል ዘ ፉል ማለቱን! ኢህአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ህልም እንዳለው ሲናገር የሰማነው ስንቴ ነው? በኋላ ስናይ ግን ነገርየው “April the fool” መሆኑ ገባን፡፡
እንዴ ተቃዋሚዎቹ እኮ መፈናፈኛ አጣን፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከለከልን፣ ልሳናችን (ጋዜጣችን ለማለት ነው) ተዘጋች፣ የተቃውሞ ሰልፍ ፈቃድ የሚሰጠን ጠፋ፣ አባሎቻችን ታሰሩ፣ መሪዎቻችን ተዋከቡ ወዘተ… እያሉ እኮ ነው፡፡ “ጠንካራ ተቃዋሚ የመፍጠር” ህልሟ ፉገራ ናት ማለት ነው - April the fool! ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በጋራ በ97ቱ ምርጫ የሰሩንንም አንረሳውም፡፡ “ሰላማዊና እንከን የለሽ ምርጫ አካሂደን ዓለምን ጉድ እናሰኛለን፣ ለቀሩት የአፍሪካ አገራት አርአያ እንሆናለን” ሲሉን አምነናቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ረብሻና ብጥብጥ፣ ግድያና እስር፣ ወከባና አፈና፣ የጐዳና ላይ ነውጥና ናዳ፣ ገዳቢ አዋጆችና መብት አፋኝ ህጐች ወዘተ ተከተሉ፡፡ የ97ቱ ምርጫ April the fool! ነበረ ማለት ነው፡፡ (ቀላል ሸወዱን!) የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች “April the fool” የሚጀምረው መቼ መሰላችሁ? ገና ሥልጣን ይዘው የመጀመሪያውን ንግግር ለህዝቡ ሲያቀርቡ ነው፡፡
ያ ንግግር ራሱ፣ “April the fool” ነው - አፍሪካ እኮ ስትጃጃል ነው የኖረችው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሃላፊዎች በቅርቡ በኢቴቪ ብቅ ብለው የውጭ ምንዛሪ በሽበሽ ነው ሲሉ ሰማሁ ልበል? ታዲያ ለምን ለባለሀብቱ አይሰጡትም? እኔማ ኢቴቪ እንደለመደው “April the fool” ሊለን ያቀናበረው ፕሮግራም መስሎኝ ነበር፡፡ በመጨረሻ ኢቴቪ እንዲያቀርብ የምፈልገውን “April the fool” ልንገራችሁና ልሰናበት፡፡ “የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ እንደሚፈቀድ የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ አስታወቀ!” የሚል ዜና እፈልጋለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ በእንዲህ ያለው ሰበር ዜና ብሸወድም አይቆጨኝም፤ ሁሌም የምመኘው ነዋ! ማሳሰቢያ:- በዚህ ዓምድ “April the fool” አንድ ቀን ብቻ ነው - አፕሪል 1፤ እሱም አልፏል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር