ኢህአዴግ የ9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ውሳኔዎች ወደ መተግበር ተሸጋግሯል -- አቶ ሀይለማርያም


አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 24 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምስት ዓመቱ የእድገትና  ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትግበራ ቀሪ ዘመን የተቀመጡ የዕድገት ግቦችን ለማሳካት ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ እንዲረባረብ የኢህአዴግ ሊቀ መንበርና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ  ህዝቦች አብዮታዊ  ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ን 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት አቶ ሀይለማርያም ፥ በጉባኤው ግብርናው በተለይም የሰብል ምርት ዕድገት የታቀደውን ያህል አለመሆን እንደ ክፍተት ተነስቶ በቀጣይ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል እንዳለበት መመልከቱን ነው የተናገሩት ።
በእቅዱ መሰረት  ምርታማነትን ለማምጣት በቀጣይ ከአርሶ አደሩ የሚጠበቀው አመለካከትን የመቀየር ጉዳይ እንዳለ ሆኖ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።
አርሷደሩን በልማት ሰራዊት በማደራጀት እንዲሁም  ከአመራርና ከባለሞያዎች ጋር በማስተሳሰር በቀሪው የእቅዱ የትግበራ ዘመን ከታሰበው በላይ ማሳካት እንደሚገባ ነው አቶ ኃይለማርያም በአፅንኦት የገለፁት ።
አገሪቱ የያዘችውን የልማትና የዕድገት ጉዞ እያደናቀፈ የሚገኘው የመልካም አስተዳደር ችግርም ቢሆን በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት አደጋው የከፋ ሊሆን  እንደሚችል  ያስረዱት አቶ ሀይለማርያም  ፥ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባትም ድርጅቱ የጉባኤውን ግማሽ ለዚሁ ለመልካም አስተዳደር ችግር ላይ አተኩሮ  መክሯል ብለዋል ።
ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ከአመራር ጀምሮ ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት በሚሆኑ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ባይ ናቸው አቶ ኃይለማርያም።
የኢህአዴግ የአመራር የመተካካትን በተመለከተ አቶ ኃይለማርያም ፥  መተካካቱ የሚፈጸመው በትውልዶች ደረጃ ነው ብለዋል።
መተካካት እንደየድርጅቶቹ ባህሪ የሚወሰን እንደመሆኑም በእኩል ደረጃ በአራቱም አባል ድርጅቶች ይካሄዳል ተብሎ እንደማይጠበቅ  ነው ያነሱት አቶ ኃይለማሪያም።
ለድርጅቱ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜም ወጣት የአመራር ትውልዶችን ልምድ ከማካፈል አንጻር ነባር አመራሮች አገልግሎታቸው ሰፊ የሚሆንበት ሁኔታም እንዳለ ተናግረዋል ።
በአጠቃላይ ግን ኢህአዴግ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ 90 በመቶ የሚሆኑ ነባር አመራሮች በሁለተኛ ትውልድ አመራሮች መተካቱን አነስተዋል ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር