19 ቁጥርና የሐዋሳው ልጅ

አዳነ ግርማ ከምርጥ አስር አፍሪካዊ ተጫዋቾች ውስጥ በመካተት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ነው፤
 
ጆሴፍ ፔፕ ጋርዲዮላ የባርሴሎናን ክለብ ማሠልጠን እንደጀመረ የመጀመሪያ ስራው ያደረገው የክለቡን ነባር ተጫዋቾች በማሰናበት በምትካቸው በዝነኛው የክለቡ ማሠልጠኛ ማዕከል ( ላሜሲያ ) ያደጉ ተጫዋቾችን በዘመቻ መልክ ማሰባሰብን ነበር።
ከነዚህ ተመላሽ ካታሎናውያን መካከል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በፈረንሳዊው አርሴን ቬንገር ለሚሰለጥነው አርሴናል አምበልና የመሃል ሜዳ አንቀሳቃሽ የነበረው ሴስክ ፋብሪጋስ ቀዳሚው ነበር።
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ተጫዋቹን ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ለማስኮብለል ከተጠቀመባቸው አማራጮች መካከል አንዱ ራሱ በባርሴሎናና በስፔን ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት ይለብሰው የነበረውን የማሊያ ቁጥር ( አራት ቁጥር ) እንደሚሰጠው ቃል መግባት ይገኝበታል።
ሜክሲኮአዊው ራፋኤል ማርኬዝ ከባርሴሎና ጋር የነበረውን ኮንትራት አጠናቆ ወደ አሜሪካው ሜጄር ሶከር ሊግ ማምራቱን ተከትሎ ተሰቅሎ የቆየውን ማሊያ አውርዶ ለወጣቱ ጨዋታ አቀጣጣይ ሲሰጠው ተጫዋቹም በተደረገለት እንክብካቤ ከፍተኛ ደስታ ይሰማው ጀመር። ምክንያቱ ደግሞ በአርሴናል ይለብሰው የነበረውን አራት ቁጥር ማሊያ በአዲሱ ክለቡ ባርሴሎናም ለብሶ መጫወት ፍላጎቱ ስለነበር ነው።
ከላይ የገለጽኩት ሐሳብ ለዕለቱ መጣጥፌ መግቢያ ይሆን ዘንድ የተጠቀምኩት ሐሳብ ነው።
የዛሬው ጽሑፌ ማጠንጠኛ የሆነው ተጫዋች ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ውቢቷ ሐዋሳ ሲሆን የመጀመሪያ ክለቡም የከተማዋ ተወካይ የሆነው ሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ነው። በዚሁ ክለብ ከተከላካይነት እስከ አማካይ መስመር ባሉት ቦታዎች ላይ የተሰጡትን ሚናዎች በሚገባ እየተወጣ ማደጉ ለአሁኑ ሁለገብ ተጫዋችነቱ ( Versatile ለመሆኑ ) የመሰረት ድንጋይ ሆኖታል።
ኢትዮጵያዊውን ኃያል ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን የማሰልጠን ዕድል ከገጠማቸው አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት ሰርቢያዊው ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ በዚህ ወጣት ክህሎትና ችሎታ ተማረኩ። በወቅቱ በክለቡ የዋሊያዎቹ የፊት አውራሪ ሳላዲን ሰኢድን ጨምሮ ሌሎች የፊት መስመር ተሰላፊዎች ቢኖሩም አሰልጣኙ ይህንን የፈረጠመ ተክለ ሰውነት ባለቤት ተጫዋች ከአማካይነት ይልቅ ወደ ፊት መስመር አመዝኖ እንዲጫወት አደረጉት።
1999 .ም የመጨረሻ ወራት ከሞቃታማዋ የመዝናኛ ከተማ ወደ አፍሪካ መዲና ኃያል ክለብ የተዘዋወረው ወጣት ከፈረሰኞቹ ጋር አራት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችንና ሌሎች ድሎችን አጣጥሟል።በግሉም ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል።
የዚህ ጽሑፍ ባለታሪክ በክለቡም ሆነ በብሔራዊ ቡድን 19 ቁጥር ማሊያ ለባሹ አዳነ ግርማ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ እግር ኳስ ተጫዋቾች ለየት የሚያደርገው የማሊያ ቁጥሩን አለመቀየሩ ሲሆን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ።
ሐዋሳ ከተማ ገብርኤል ሰፈር ተወልዶ ማደጉ ተጫዋቹ የማሊያ ቁጥሩን እንዲመርጥ እንዳደረገው በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህ ተጫዋች በስኮትላንዳዊው ኤፊም ኦኑራ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ወቅት ለዋሊያዎቹ መሰለፍ ቢጀምርም በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ግን በጣም ጎልቶ ወጥቷል።።
የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚወስደውን የአውሮፕላን ቲኬት ከመቁረጡ በፊት የነስቴፈን ሴስንሆን አገር ቤኒንንና ጎረቤታችንን ሱዳንን ማሸነፍ ግድ ይለው ነበር።ለዚህ ደግሞ የእንግሊዙ ሰንደርላንድ እግር ኳስ ክለብ ፈጣን አጥቂ የሆነውን ሴስንሆን አካቶ አዲስ አበባ የመጣው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቤኒን ብሔራዊ ቡድን ግብ ሳይቆጠርበትም ሳያስቆጥርም ወደ አገሩ ተመለሰ።
ዋሊያዎቹ በዚህ ጨዋታ ባስመዘገቡት ውጤት የተከፋው ደጋፊ ሐዘኑ ቢበረታበትም የመልሱ ጨዋታ በአገሪቱ መዲና ፖርቶ ኖቮ ሲካሄድ 19 ቁጥር ለባሹ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣዩ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ አሳለፈች።
በካሜሩናዊው ዳኛ ጉልህ ስህተት እና በተከላካዮቻችን የትኩረት ማነስ ምክንያት ካርቱም ላይ አምስት ለሦስት ኢትዮጵያ ብትሸነፍም ብሔራዊ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች መካከል አንዷ በአዳነ ግርማ ግንባር ተገጭታ የተቆጠረች ነበረች።
የመልሱ ጨዋታ ከአንድ ወር በኋላ በአዲስ አበባ ሲደረግ ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ዋሊያዎቹ ሁለት ማስቆጠር የግድ ይላቸው ነበር።በራዲሰን ብሉ ሆቴል የመሸገውና በውጤታማው አሰልጣኝ የመሐመድ ማዝዳ የሚሰለጥነው የሱዳን ቡድን በእድሜ ባለጸጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ለሚያደርገው ጨዋታ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓትና ከዚያም በፊት ጀምሮ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት ለማግኘት ያደረው ደጋፊ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ስዩም ከበደ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታ መከፋቱን መግለጽ ሲጀምርና ወደ ተስፋ መቁረጥ ሲገባ ይህ የደቡብ ልጅ የቡድኑን መንፈስ ያነሳሳች ግብ በማስቆጠር እንግዳውን ቡድን ጭንቀት ውስጥ አስገባው።ለዚች ግብ መገኘት የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ከበሬታ አስገኝቶለታል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘውና የቀድሞ የክለብ አጋሩ የነበረው ሳላዲን ሰኢድ ዋሊያዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው እርግጥ መሆኑን ያበሰረችዋን ወሳኝ ግብ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ የደደቢቱ አዲስ ሕንጻ አስተዋጽዖ እንዳለ ሆኖ አዳነ ግርማም ድርሻው ከፍተኛ ነበር።
ብሔራዊ ቡድኑ በአራት የማጣሪያ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ተቆጥረውበት ሰባት ሲያስቆጥር 19 ቁጥር ለባሹ አዳነ ግርማ ሦስት ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል።
የአውሮፓውያኑ 2011/2012 የውድድር ዘመን አፍሪካ ውስጥ ከሚጫወቱ አፍሪካውያን ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ውስጥ ስሙ የሰፈረው የፈረሰኞቹ አጥቂ ከመጨረሻዎቹ አስር ምርጦች አንዱ በመሆን የመጀመሪያው የአገራችን ተጫዋች ሆኗል።
ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛው ዙር ሲያልፍ ወደ ማሊ ባማኮ በጉዳት ምክንያት ያልተጓዘው አዳነ ግርማ ከ19 ቁጥር ማሊያ ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ነው።1999.ም አስራ አንድ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ተወዳዳሪ ለሌለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረመውና በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብቸኛዋን የአገራችንን ግብ በዛምቢያ ላይ ያስቆጠረው ተጫዋች በ19 ቁጥር ማሊያው ታሪክ መስራቱን እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር