መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን የቅስቀሳ ፕሮግራም በተገቢው መንገድ ሊያስተናግዱ ይገባል

አዲስ አበባ የካቲት 27/2005 መገናኛ ብዙሃን በ2005 ዓ.ም ለሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን የቅስቀሳ ፕሮግራም በተገቢው መንገድ እንዲያስተናግዱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጪው መጋቢት 4 ቀን እስከ ሚያዚያ 4/2005 ድረስ ለሚያቀርቡት የምርጫ ቅስቀሳ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል በዕጣ ተከናውኗል፡፡ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት መገናኛ ብዙሃን ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን የቅስቀሳ ፕሮግራም ህግና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት በአግባቡ ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ድልድሉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባፀደቀው መመሪያ መሰረት መከናወኑንና 50 በመቶ ሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የሚካፈሉት ሆኖ 30 በመቶ በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች ባላቸው ብልጫ፣ 20 በመቶውን ጊዜ ደግሞ ባቀረቡት እጩ ተወዳዳሪ ብዛት የሚጠቀሙ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሰረትም 24ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሬዲዮ 19 ሠዓት ከ20 ደቂቃ፣ በቴሌቪዥን 12 ሠዓትና በተለያዩ ጋዜጦች 48 አምዶችን ያለምንም ክፍያ የምርጫ ቅስቀሳቸውን እዲያካሂዱ መደልደሉን ተናግረዋል፡፡ ለዚሁ ስራ የተመደበው የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ በገንዘብ ሲተመን ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያህል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይህም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፖሊሲያቸውን፣ ስትራቴጂያቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህብረተሰቡ በነጻነት እንዲያቀርቡ መንግሥት ካለው ቁርጠኝነት አንጻር የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች ልምድ እንደታየው የተመደበላቸውን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ያለመጠቀም ችግር መታየቱን ያስታወሱት አቶ ልዑል ፓርቲዎች የተሰጣቸውን እድል በአግባቡ በመጠቀም ለመራጩ ሕዝብ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል፡፡ በቅስቀሳቸው ወቅትም የተለያዩ ህጎችና አሰራሮችን በተከተለና ሕገ መንግሥቱን ባከበረ መልኩ ፕሮግራማቸውን በተመደበላቸው ጊዜ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳቸውን በሚያቀርቡበት ሂደት ችግር ቢያጋጥማቸው ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ቅሬታቸውን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የቅንጅት ፓርቲ ዋና ፀሃፊና እጩ ተወዳሪ አቶ ሳሳሁልህ ከበደ ድልድሉን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ከምርጫ 97 ጀምሮ የነበረው ድልድል በፓርላማ መቀመጫና በእጩ ተወዳዳሪ ብዛት እንደነበረ አስታውሰው አሁን ኢህአዴግ ፓርቲዎችን ለማበረታታት ያደረገው 50 በመቶውን የአየር ጊዜ በእኩል የማከፋፈል አሰራር የተሻለ ነው፡፡ እንደ ቅንጅት ፓርቲ ካለፉት ሶስት ምርጫዎች አኳያ የተሻለ የዕጣና የድልድል ወቅት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሳሳሁልህ ፓርቲዎች በቀጣይ አገራዊ ምርጫዎች እንዲሳተፉ የሚያነሳሳና በመገናኛ ብዙሃን የመጠቀም እድላቸውንም የሚያሰፋ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው ደግሞ ውድድሩ ምንም እንኳን ገዥው ፓርቲ በመላ አገሪቱ እጩዎችን ያቀረበ በመሆኑና ባለው የፓርላማ ወንበር ብዛት ምክንያት የመገናኛ ብዙሃንን የመጠቀም እድሉ የተራራቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ''የተሰጠን የአየር ሠዓት ከመራጮቻችን ጋር ለመገናኘት የፈለግነውን ያህል ባይሆንም በጥቂቱ ደህና ነው ማለት ይቻላል'' ሲሉ አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሠላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሠይድ ይመር ዓሊ በበኩላቸው የተሰጠው የአየር ሠዓትና የጋዜጦች አምድ በቂ ባይሆንም ልምዱ ግን ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ውጤት እንደሚኖረው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ጅምሩ ሊቀጥል የሚገባውና የሚበረታታ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በአራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ አምስት ጋዜጦችና 13 የሬዲዮ ጣቢያዎች በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ሶማሊኛና ሀረሪ ቋንቋዎች እንደሚያካሂዱ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር