ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሊያስገኝ የሚችለው ቀርከሃ


በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት የሚሸፍን ቀርከሃ አለ ተብሎ ይታመናል፡፡ በየዓመቱም እስከ 12 ሚሊዮን ቶን የሚገመት የቀርከሃ መጠን ለተለያዩ ምርቶች ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል በዘርፉ የተደረገ ጥናት ያመለክታል፡፡
ሀብቱ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ቢውል ደግሞ ለ500 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ከ500 ሚሊዮን እስከ 700 ሚሊዮን ብር ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ምርት በየዓመቱ ማምረት እንደሚቻል ሰሞኑን በአፍሪካ የቀርከሃ ሀብት ዙሪያ የተደረገ ዓውደ ጥናት ላይ ተጠቅሷል፡፡

ቀርከሃ በየዓመቱ በብዛት ሊበቅል የሚችል ተክል ሲሆን በአግባቡ ከተያዘና ከተጠበቀ ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በተጨማሪ ምርቱን ሳያቋርጡ ለዓመታት ማግኘት እንደሚቻል ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ቀርከሃን በመቀጠም በኢትዮጵያ የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ መጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. በተካሄደ ዓውደ ጥናት ላይ ማብራሪያ ቀርቦ ነበር፡፡

ዓውደ ጥናቱን አስመልክቶ በቀርከሃ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችን ያቀረበው መረጃ በቀርከሃ የተሠሩ 200 ሺሕ ቤቶች ለገጠሩ ኅብረተሰብ በግልና በሰፈራ መሥራቱን ያስታውሳል፡፡ በገንዘብ ሲሰላ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋም አስፍሯል፡፡ በቀርከሃ የተሠሩ 700 ሺሕ የቤት ቁሳቁስ መሣሪያዎች የተመረቱ ሲሆን፣ ከ20 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ያትታል፡፡ በዚሁ መረጃ መሰረት፣ 250 ሺሕ ቶን ቀርከሃ ለማገዶ መዋሉን፣ በገንዘብ ሲመዘንም ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ 45 ቶን ቀርከሃ ለከብቶች መኖነት መዋሉ ከመገለጹም ባሻገር፣ በአዲስ አበባና አሶሳ የተከፈቱ ሁለት ፋብሪካዎች እስካሁን ድረስ ከ30 ሺሕ ቶን በላይ የቀርከሃ ምርትን ለተለያየ አገልግሎት ማዋላቸውም ተዘርዝሯል፡፡ የሚያመርቱት ውጤት በገንዘብ ሲሰላም ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ተገምቷል፡፡

እንዲህ የተነገረለትን ቀርከሃ፣ ኢትዮጵያ በአግባቡ አልተጠቀመችበትም፡፡ የቀርከሃ ምርትን ግብዓት በማድረግ በዘመናዊ ኢንዱስትሪ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት አልተቻለም፡፡ ቀርከሃን ጥሬ ዕቃ አድርገው የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ቁጥር ሁለት ብቻ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ግን ይህንን ምርት በአግባቡ ለመጠቀም ብዙ ሥራዎች ተሠርቷል ይላል፡፡

በቀርከሃ ልማት፣ አጠቃቀምና ምርት ላይ እንዲሁም በቀርከሃ ምርት ሥራ ላይ ለ2,500 ሰዎች በተግባር የተደገፉ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸው ተገልጿል፡፡

ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆኑ 15 ዓይነት የቀርከሃ ዝርያዎች ከቻይና፣ ከህንድና ከደቡብ አሜሪካና ከሌሎች አገሮች በማስገባት፣ በማላመድና በማባዛት እንዲተከሉ መደረጋቸውን፣ በግብርና ሚኒስቴር ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መላኩ ታደሰ ይገልጻሉ፡፡

ዘመናዊ የቀርከሃ ከሰል አመራረትና አጠቃቀም ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የተለያዩ አነስተኛና ጥቃቅን ማኅበራትን በማደራጀትና በማሠልጠን የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የቀርከሃ ኢንዱስትሪን ለማቋቋም አንድ ሔክታር መሬት በቂ ነው የሚሉት የቀርከሃና ራታን መረብ ድርጅት፣የምሥራቅ አፍሪካ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሁንዴ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ የምትሆንበትን የተለያዩ ሥራዎች እየሠራች ሲሆን 10 ዘመናዊ ፋብሪካዎች ቢቋቋሙ እንኳ፣ ጥሬ ዕቃው ከበቂ በላይ ያገኛል ብለዋል፡፡ ብዙ ሊሠራበት ይችላል ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከቀርከሃ በቀላሉ የሚሠራው ጥርስ መጐርጐሪያ (ስቴኪኒ) እንኳ ከውጭ መግባት እንዳልነበረበት የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ፣ በበቂ ሁኔታ እዚህ ሊመረት ይችል ነበር ይላሉ፡፡

በዓውደ ጥናቱ ላይ እንደተጠበቀሰውም የቀርከሃ ሥነ ሕይወት፣ አስተዳደግ፣ አመራረትና አጠቃቀም ላይ የተለያዩ ጥናቶች እንዲካሄዱ በማድረግ ከሰባት በላይ መርጃ መመሪያዎች በማሳተምና በማሠራጨት ሥራ ላይ መዋሉንም ዘርፉን ለማሳደግ ከተደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው ተብሏል፡፡

ቀርከሃ አማራጭና ታዳሽ ኃይል በመሆን ለማገዶና ለከሰል አገልግሎት እንደሚውል በጥናት ተረጋግጦ በጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል፣ የቀርከሃ እንቡጥ (Bamboo Shoot) ለምግብነት የሚውል ሲሆን እስካሁን ድረስ ግን በአገራችን ጥቅም ላይ የዋለው ከ3 እስከ 5 ቶን ያለው ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ወደፊት ለምግብነት እንዲውል፣ መሥራት እንደሚገባም ተመክሮበታል፡፡

እንደዓውደ ጥናቱ አዘጋጆች ገለጻ፣ ዓውደ ጥናቱ በአጠቃላይ የዘርፉ ልማትና አጠቃቀም በአገር ብሎም በአኅጉር ደረጃ እንዲሻሻልና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲደረግበት የአገሮች ትብብር፣ ትስስርና ቅንጅት የጎላ ድርሻ እንዲኖረው ፈር የቀደደ ነው፡፡

በአፍሪካ ውስጥ ቀርከሃ በተፈጥሮው ሰው ሰራሽ ዘዴ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ያለውን የቀርከሃ -ብት ብዛትና ዓይነት በአፍሪካ አኅጉር ብሎም በዓለም እንዲታወቅ የሚደረግበትን ሁኔታ በማመቻቸቱ ረገድ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል፡፡ በአኅጉሩ ውስጥ ይህ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም በአሁኑ ጊዜ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ሌሎች የእስያ አገሮች የደረሱበትን የቀርከሃ ቴክኖሎጂ ምጥቀት ልምድ ለመቅሰምና ሽግግር ለማድረግ የሚቻልበትን ዘዴም ይመቻቻል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ከሰሐራ በታች ባሉ አገሮች ሦስት ሚሊዮን ሔክታር የሚሸፍን የቀርከሃ ደን እንደሚገኝ ሲታወቅ፣ ከአጠቃላይ የቀጣናው የደን ሽፋን የአራት በመቶ ድርሻን የያዘ ነው፡፡ በዓለም ላይ የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ድርሻ ያለው የቀርከሃ ሀብት፣ በአግባቡ ቢሠራበት ለአፍሪካ የወጪ ንግድ አስተዋጽኦ ከማድረግ በላይ፣የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እንደሚረዳ ይታሰባል፡፡  

የቀርከሃ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ተቀባይነት እየጎላ መምጣቱን ለውጭ፣ ለአገር ውስጥ ንግድና ለብዙኀኑ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በአውደ ጥናቱ የቀረቡ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የቀርከሃና ራታን መረብ ድርጅት ምክር ቤት ሊቀመንበር ሆና መመረጧን የገለጹት አቶ መላኩ፣ በአኅጉሩ ያላትን ከፍተኛ ኃላፊነት፣ ከመወጣት አኳያ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ተቀርፆላቸው ሊሠሩ የታቀዱ ዋና ዋና የተባሉ ተግባራት እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፣ በዚህ ዕቅድ መሠረት በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቻይና መንግሥት በተገኘ ድጋፍ አንድ ተቋም ይቋቋማል፡፡

ከዚህም ሌላ በአሁኑ ጊዜ የግብርና ሚኒስቴር ዋና ዋና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ አንድ ዓብይ ኮሚቴ በማቋቋምና በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊሠሩ ከታቀዱ ሥራዎች መካከል የቦታኒካል ጋርደን ማቋቋም፣ የቀርከሃ ቦታ መከለልና በተሻሻለና ሳይንሳዊ በሆነ አያያዝ መጠበቅ የዕቅዱ አካል ነው፡፡

ቀርከሃ ላይ እሴት የመጨመር ሥራዎች፣ የአቅም ግንባታ መመሪያዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን መከለስና ማዘጋጀት፣ ምርምርና ልማት ማካሄድ፣ ችግኝ ጣቢያ ማቋቋም፣ ነባር የቀርከሃ ደኖችን መልሶ ማልማትና አዲስ ተከላ ማካሄድ፣ በቀጣይነት ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የልማት የትብብር መስኮችን በመለየት በፕሮግራመችና ፕሮጀክቶች የተደገፉ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማካሄድ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ የሚቻል መሆኑንም ባለሙያዎቹ አመልክተዋል፡፡

የግል የቀርከሃ አምራች ፋብሪካዎች ቁጥርም እየጨመረ ለመምጣቱ፣ አገር በቀልና የውጭ ባለሀብቶች በቀርከሃ ኢንዱስትሪው ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት ሒደት ላይ መገኘታቸው ዋቢ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀርከሃ ኢንዱስትሪ ከተሰማሩ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የአደል ኢንዱስትሪስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳነ በርሔ፣ ከቀርከሃ የማይመረት ነገር እንደሌለ፣ ከሚመረቱት ውስጥ  የቤት ቁሳቁሶች፣ ጣውላዎች፣ ከሰል፣ ስቴኪኒ፣ ምንጣፍና ሰንደል የመሳሰሉት ምርቶች ሰፊ ገበያ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

የምርት አቅርቦቱን በቴክኖሎጂና በአዳዲስ አሠራሮች በመደገፍ በዓለም ገበያ ሊሸጡ የሚችሉ ምርቶች ማቅረብ ከተቻለ፣ ለዘርፉ ምቹ የሆነ ሥነ ምኅዳር በኢትዮጵያ በመኖሩ የቀርከሃ ተፈላጊነት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ይታሰባል፡፡

በኢትዮጵያ የተስተናገደውና የአፍሪካ የቀርከሃ ምርትን በተመለከተው ዓውደ ጥናት ላይ የቀረቡ ጥናቶች፣ በግብርና ሚኒስቴርና ዓለም አቀፍ የቀርከሃና ራታን ኔተዎርክ ዋና አዘጋጅነት እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅትና ከካናዳ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር