በደቡብ ክልል ትምህርት ቤቶች መካከል ሲካሄድ የቆየው የስፖርት ውድድር በሲዳማ ዞን ትምህርት ቤቶች የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡


በውድድሩ በክልሉ 11 ዞኖች፣ ሶስት ልዩ ወረዳና በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ ከ250 የሚበልጡ የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ከ3ሺህ በላይ ወንድና ሴት ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡


በውድድሩ የሲዳማ ዞን ትምህርት ቤቶች በጤረጴዛ ኳስ፣ በአትለቲክስ ወንዶችና ሴቶች በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ በመሆን ሰባት ዋንጫዎችን ወስደዋል፡፡


የካምባታ ጣምባሮ ዞን ትምህርት ቤቶች ደግሞ በእጅ ኳስ ወንዶችና ሴቶች፣ መረብ ኳስ ሴቶች ሶስት ዋንጫ በማንሳት ዞኑ ውድድሩን በሁለተኛነት እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል፡፡


የጉራጌ ዞን ትምህርት ቤቶች ቅርጫት ኳስ በሁለቱም ፆታ አሸናፊ በመሆን ዞኑ በሶስተኛ ደረጃ ውድድሩን እንዲያጠናቅቅ ያደረጉት ሲሆን የሰገን አከባቢ ህዝቦች ዞን ትምህርት ቤቶች በእግር ኳስ፣የወላይታ ዞን በወንዶች መረብ ኳስ አሸናፊ በመሆን አንዳንድ ዋንጫ ወስደዋል፡፡


የሀዲያ ዞን ትምህርት ቤቶች ከመጀመሪያው እስከ ፍፃሜው ባሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነት የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡


ከየካቲት 10 እስከ 21/ 2005 በተካሄደው ውድድር ክልሉን ወክለው በአዲስ አበባ በሚካሄደው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር የሚሳተፉ ከ400 በላይ ስፖርተኞች ተመርጠዋል፡፡


የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ ለውድድሩ አሸናፊዎች፣ ለኮከብ ዳኞች፣ ተማሪዎች፣ለውድድሩ መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዋንጫ፣ ሜዳሊያና ምስክርወረቀት ካበረከቱ በኃላ እንደገለጹት ስፖርት ለአንድ አገር ማህበራዊና ኢኮኖሚ እድገት ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ በብሄር ብሄርሰቦች መካከል ያለውን አንድነትና የባህል ትስስር ለማጠናከር የላቀ ሚና አለው፡፡


መንግስት ይኸንን በመገንዘብ ከሁሉም የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የስፖርቱን እንቅስቃሴ ለማሳደግ፣ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና የወጣቱን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጎልበት የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡


በተለይም ትምህርት ቤቶች የወጣቱ መገኛና የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ ቁልፍ ማዕከል በመሆናቸው መንግስት በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የስፖርቱን እንቅስቃሴ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ አንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ አህመዲን በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በአፍሪካና በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ለገፅታ ግንባታ ስራችን ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱ የተተኪ ስፖርተኞች ምንጭ መሆናቸውን ያሳዩበት ውድድር ነው ብለዋል፡፡


በክልሉ እየተገነባ ያለውን የትምህርት ልማት ሰራዊት በትምህርት ቤቶች መካከል በሚደረገው ስፖርታዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ውድድሩ ዋነኛ መድረክ ከመሆኑም ባሻገር ታዳጊ ተማሪዎች የየአከባቢያቸውን ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊቶች በመለዋወጥ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት አጠናክረው ለማስቀጠል ቁልፍ ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡


ምነጭ ኢዜአ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር