የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ እናደርጋለን የሚለው ውሳኔ ነው


አራቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች በተናጠልም በጋራም ባካሄዱት ድርጅታዊ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን አላልፈዋል፡፡ ውሳኔዎቹን ተግባራዊ እናደርጋለን ብለውም ቃል ገብተዋል፡፡
ያለፈውን ጉዞ በመገምገም አዲስ ዕቅድ ካለም በማፅደቅ ተግባራዊ መሆን ያለባቸውን በመወሰን ተግባራዊ እናደርጋለን ማለት በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚደረግና የተለመደ ትክክለኛ አሠራር ነው፡፡ መወሰንና ውሳኔውን ተግባራዊ እናደርጋለን ማለቱ ላይ ምንም ተቃውሞ የለንም፡፡ ድጋፍ እንጂ፡፡

ከውሳኔዎች ሁሉ የበላይ የሆነው ውሳኔ ግን አለ፡፡ እሱንም ተግባራዊ እናደርጋለን ብላችሁ በይፋ ተናገሩ፣ አውጁ፣ ቃል ግቡ ብለን ደግመን ደጋግመን እንማፀናለን፡፡ የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ የምንለው ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ እናደርጋለን የሚለው ውሳኔ ነው፡፡

ሕገ መንግሥታችን ለፍትሕ የቆመ ነው፡፡ ነገር ግን በተግባር ሲታይ የፍትሕ አካላት እየተዳከሙ፣ ገንዘብ፣ ጉቦና ሌላ ጥቅማ ጥቅምና ጣልቃ ገብነት እያዘቀጣቸው ይገኛል፡፡ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተጠብቆ የተሟላ ፍትሕ እያገኙ አይደሉም፡፡ ከሕገ መንግሥት ተገዥነት በላይ የግል ጥቅም ተገዥነት የበላይነት እየያዘ ነው፡፡

ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ ይጠብቀናል ብሎ መተማመን የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው፡፡ ባለገንዘብ የሆነ ወንጀለኛ አይነካም፣ ያመልጣል፣ ይፈራል፣ ሕግ ጠባቂዎችን ያንበረክካል፣ ፍትሕ ሰጪዎችን ይገዛል፣ ሕገ መንግሥቱን ያረክሳል፡፡

ሕገ መንግሥታችን ለመልካም አስተዳደር የቆመ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ግን በእጅጉ እየተጓደለ፣ እየተረሳና እየተረገጠ ነው፡፡ ጭራሽ አቤት የሚባልበት እየታጣ ነው፡፡ የሕዝብ አገልጋይ ተብሎ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው አስተዳደር ፀረ ሕዝብ እየሆነና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅም የሚገዛው ሆኗል፡፡ የተቦረቦረ፣ የተሸረሸረና የተቸረቸረ መዋቅር እየሆነ ነው፡፡

ይህ ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ ይጠብቀኛል ብሎ ሕዝቡ መኩራራትና መተማመን አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ዋስትና የሰጠው መልካም አስተዳደር ፀረ ሕገ መንግሥት በሆነ አደገኛ ማጭበርበር ተተክቷልና፡፡ ሕገ መንግሥታችን በማያሻማ መንገድ ለሰብዓዊ መብት የቆመ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ግን እየተጣሰ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሚመለከታቸው መስተካከልና መታረም ያለበትን እየጠቆሙ ነው፡፡ ሥጋት የሚያስከትሉ ችግሮች ስለታዩ፡፡ ሕገ መንግሥቱን እናክብራለን የሚል ውሳኔ በከፍተኛ ደረጃ እንዲስተጋባና እንዲተገበር የምንፈልግበት ዋነኛው ምክንያት ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ነው፡፡

የፕሬስ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በማያሻማ መንገድና ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ ሁኔታ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የወጡ አዋጆችም ሚዲያ በአገራችን እንዲስፋፋ የሚያደርጉና የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም እንዲያብቡ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በተግባር ግን አንድም የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የለም፡፡ የመንግሥት ሞኖፖሊም በዚህ መስክ በእጅጉ ተጠናክሯል፡፡ በግል ሕትመት ዘርፍም ሥራን በአግባቡ ለማከናወን ትልቅ ፈተና የሆነበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ማሽን ተበላሽቷል በሚል ምክንያት ጋዜጦችና መጽሔቶች ለአንባቢያን አልደርስ ሲሉ፣ መረጃ ማግኘትም ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው ብሎ የሚሟገት መንግሥታዊ አካል ጠፍቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚገኝ የግል ፕሬስ ያለባት አገር ሆናለች፡፡

ለዚህም ነው አሁን ትናንትም ደግመን ደጋግመን ሕገ መንግሥቱን እናከብራለንና እንተገብራለን የሚለው የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ ውሳኔ ይሁን የምንለው፡፡ ሕገ መንግሥታችን ባለሥልጣናት አገርንና ሕዝብን እንዲያገለግሉ፣ የሕዝብን አደራ በማስቀደም ኃላፊነት የሚሸከሙ ዜጎች እንዲሆኑ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በተግባር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዎችንና ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ባለሥልጣናት ቢኖሩም፣ በዚያው መጠን ሳይሆን ከዚያ በባሰ ደረጃና መጠን ግን አገርንና ሕዝብን ማገልገል ረስተው ግለሰቦችን የሚያገለግሉ፣ ለጥቅም የሚገዙ ተላላኪዎችና ጥገኞች እንዳሉ ሕዝብ በግልጽ የሚያውቀውና በዓይነ ቁራኛ እየታዘበና እየተከታተለው ያለ ጉዳይ ነው፡፡

ባለሥልጣናት ሥነ ምግባር ኖሯቸውና ለሕገ መንግሥት ተገዥ ሆነው ሕዝብንና አገርን እንዲያገለግሉ ነው ሕገ መንግሥታችንን እናከብራለንና እንተገብራለን የሚለው የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ ውሳኔ ይሁን የምንለው፡፡ ሕገ መንግሥታችን በሃይማኖት ነፃነት ያምናል፡፡ አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው ይላል፡፡ ሁሉንም ሃይማኖቶች በእኩል ያያል፡፡ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ናቸው ይላል፡፡ ይህንን መብት እያንዳንዱ ዜጋ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ከማንኛውም አቅጣጫ የሚመጣ ጫናም ይሁን ጣልቃ ገብነት ይህን መብት እንዳይጋፋ መንግሥት መረባረብ አለበት፡፡ ከመንግሥትም፣ ከባለገንዘብም፣ ከውስጥም፣ ከውጭም ይህንን መብት የሚጋፋ እንዳይኖር መከላከልና መጠበቅ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱን እናከብራለንና እንተገብራለን የሚለው የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ ውሳኔ ይሁን የምንልበት ሌላው ምክንያትም ይኼው ነው፡፡

ስለመፈክርና ስለመዝሙር አይደለም እያወራን ያለነው፡፡ ስለተግባር ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን እናከብራለን የሚል መፈክር በየግድግዳው ሊጻፍና ሊለጠፍ ይችላል፡፡ በተግባር ግን ሲረሳ፣ ሲዘነጋና ሲረገጥ እየተስተዋለ ነው፡፡

ለሕገ መንግሥቱ ተግባራዊነት መቆም ልዩ ትኩረት ይሰጠው እያልን ያለነው ነገ አገራችን ለአደጋ ተጋልጣ በታሪክ የምንወቀስበትና የምንከሰስበት ሁኔታ ላይ ልንገኝ ስለምንችል ነው፡፡ ካለ ጨረታና ካለ የታሸገ ኤንቨሎፕ ሕገ መንግሥቱንና ሕጎችን ገዝተናል፣ ተቆጣጥረናል የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ኔትወርኮች ተፈጥረዋል፡፡ ለሕገ መንግሥት መቆም ያለበት ሁሉ ለእነዚህ እየሰገደ ይገኛል፡፡ ይህ አካሄድ ልንወጣው ወደማንችለው ውርደት፣ ኃፍረትና ውድቀት ያመራናልና እንጠንቀቅ! እንንቃ! እንረባረብ!

ሁሌም ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ ላይ እንወያይ እንወስን፡፡ ነገር ግን የውሳኔዎች ሁሉ የበላይ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን ማክበርና መተግበር ነው!  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር