በሚቀጥለው ሳምንት የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ስብሰባ ይጀምራሉ


አራቱ የኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የየራሳቸውን ጠቅላላ ጉባዔ ይጠራሉ፡፡ በተናጠል የሚጠሩት የፓርቲዎቹ ጠቅላላ ጉባዔዎች ቀጣዮቹን የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ይመርጣሉ፡፡
በእነዚህ ጉባዔዎች የሚመረጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ደግሞ ብሔራዊ ፓርቲያቸውን ወክለው ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚሆኑ ሰዎችን ይመርጣሉ፡፡ ብአዴን፣ ደኢሕዴግ፣ ኦሕዴድና ሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከመጋቢት 14 እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚካሄደው የእናት ፓርቲያቸው (ኢሕአዴግ) ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ባህር ዳር ከተማ ይከታሉ፡፡ 

በዚህ የኢሕአዴግ ዘጠነኛ ጉባዔ ላይ ትኩረት ከሚያገኙ አጀንዳዎች መካከል የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ አዳማ ከተማ ተስብስቦ ያፀደቃቸውን ዕቅዶች አፈጻጸም፣ በተለይ አዳማ ላይ ለተካሄደው ጉባዔ የቀረበው የሁለት ዓመት የፓርቲው ዕቅድ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መነሻ በመሆኑ በጥልቀት ይገመገማል ተብሏል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ነባር ታጋዮችን (አመራሮችን) በመተካካት መርሐ ግብሩ እየቀነሰ በወጣት ኃይል ለመተካት የተያዘውንም ዕቅድ ይገመገማል፡፡ የብአዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለምነህ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በብአዴን ደረጃ መተካካቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እየሄደ ነው፡፡ የተለወጠ ነገር የለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የአራቱ ፓርቲዎች የበታች አመራሮች በስብሰባ ተጠምደዋል፡፡ ይህ የፓርቲዎቹ የታችኛው መዋቅር ስብሰባ የሚወክሉ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን መርጦ ይልካል፡፡ የተመረጡት የፓርቲዎቹ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣሉ፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴዎቹ ናቸው ቀደም ሲል ዘጠኝ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን የሚልኩት፡፡ በመተካካት ፖለቲካው በርካታ የሕወሓትና የብአዴን ነባር ታጋዮች ከሥራ አስፈጻሚ አባልነት መሰናበታቸው ይታወቃል፡፡ 

ቀሪዎቹ ነባር አመራሮች ባህር ዳር በሚካሄደው ጉባዔ ይተካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ፡፡ በባህር ዳሩ ጉባዔ 1,600 አባላት በኢሕአዴግ ይወከላሉ፡፡ ከግንባሩና ከሌሎች ድርጅት በተጨማሪ 900 ተጋባዥና ታዛቢ እንግዶችን ጨምሮ በድምሩ 1,500 ሰዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ 42 ምሁራንና 15 የሌሎች አገሮች የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡ 

ባህር ዳር ይህንን ጉባዔ የምታስተናግደው የክልሉ ምክር ቤት ከ415 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ እያስገነባ በሚገኘው ግዙፍ ሕንፃ ውስጥ ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ በልዩ ዘዴ ተጠልፎ በሕንፃ ውስጥ የሚያልፍ ሲሆን፣ ሕንፃው በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የሚል እምነት ተይዟል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር