የሲዳማና የምዕራብ አርሲ አጎራባች ነዋሪዎች የጋራ ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየተሰራ ነው

አሰላ መጋቢት 18/2005 የሲዳማና የምዕራብ አርሲ ዞኖች አጐራባች ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን የሁለቱ ዞኖች አስተዳደሮች አስታወቁ፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ አጐራባች ወረዳዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ተወካዮች በግጭት አፈታትና በሰላም ባህል ግንባታ ዙሪያ የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የሁለቱ ዞኖች አስተዳደር የጸጥታና አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊዎች አቶ ሳሙኤል ሼባና አቶ ሁሴን ፈይሶ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአጎራባች ወረዳዎች ከግጦሽ ሳር፣ ከውሃና ከቦታ ይገባኛል ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ለመፍታት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በደቡብ ሲዳማ ዞንና በኦሮሚያ ምዕራብ አርሲ ዞን በሚገኙ ሰባት አጎራባች ወረዳዎች የነበሩት አለመግባባቶች በጋራ በመፍታት እየተሻሻለ የመጣውን ለውጥ ዘላቂ በማድረግ በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የህዝቡን የጋራ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል፡፡ ለግጭትና አለመግባባት መንሰኤ የሆኑትን ችግሮች በመለየት በርካታ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀው ስልጠናም የዚሁ ጥረታቸው አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመው የህዝብ ለህዝብ ትስስርና መልካም ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ትኩረት ሰጥተው በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ የደቡብ ክልል ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አርኮ ደምሴ በበኩላቸው ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን በተለይ በአጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ችግራቸውን በመግባባት ፈተው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ሁለቱ ክልሎች በጋራ ባዘጋጁት ስልጠና ላይ ከሲዳማና ከምዕራብ አርሲ ዞኖች ከሚገኙ ሰባት አጎራባች ወረዳዎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ 150 የማህበረሰብ ተወካዮች መሳተፋቸውንም አቶ አርኮ አመልክተዋል፡፡ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ስልጠና ላይ በግጭት አፈታትና በሰላም ባህል ግንባታ ከአሁን ቀደም በተከናወኑ በርካታ ተግባራት ላይ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችና ልምድ በመለዋወጥ ተመልሰው ለወከላቸው ህዝብ በማድረስ የጋራ ተጠቃሚታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚስችላቸው ትምህርት እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር